Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

‘የኤርትራ ወታደር ጥቃት እያደረሰብን ነው’ በሚል በደብረፂዮን ገብረሚካኤል የተሰጠው መግለጫ ፍፁም ሃሰት ነው – ሜጀር ጄነራል መሐመድ ተሰማ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 1፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ‘የኤርትራ ወታደር ጥቃት እያደረሰብን ነው’ በሚል በደብረፂዮን ገብረሚካኤል የተሰጠው መግለጫ ፍፁም ሃሰት መሆኑን ሜጀር ጄነራል መሐመድ ተሰማ ገለፁ።

ሜጀር ጄነራል መሐመድ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፥ ጁንታው በተለያዩ አጋጣሚዎች ለማደናገር ጥረት እያደረገ ይገኛል።

ጁንታው ቀደም ሲል “በቂ ተዋጊ አለኝ፣ ሰሜን አዝም አብሮን ተሰልፏል፣ የመከላከያ ሃይሉን የጦር ጀቶች በሚሳኤል እንመታለን” የሚል ፉከራ ውስጥ እንደነበረ አስታውሰዋል።

‘የትግራይ ምድር ለሚዋጉን ሁሉ መቀበሪያ ትሆናለች’ የሚል ዛቻም ያሰማ እንደነበር ገልጸዋል።

“አሁን ያ ሁሉ ፉከራ ነገር አልሳካ ብሎ በመከላከያ ሃይሉ አከርካሪው እየተሰበረ ሲመጣ ሌላ የማደናገሪያ ሃሳብ ይዞ ብቅ ብሏል” ሲሉ ተናግረዋል።

በመሆኑም ‘አሁን ላይ የኤርትራ ወታደር ጥቃት እያደረሰብን ነው’ በሚል በደብረፂዮን ገብረሚካኤል የተጠው መግለጫ ፍፁም ሃሰት መሆኑን ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ ፅንፈኛ ቡድኑ በሚያሰራጫቸው የሃሰት ወሬዎች እንደይደናገርም መክረዋል።

በፅንፈኛ ሃይሉ ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ አሁንም ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸው “በቅርቡም በርካታ የድል ዜናዎችን ለኢትዮጵያ ህዝብ እናበስራለን” ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

Exit mobile version