Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በመዲናዋ የኤሌክትሪክ አውቶብስ የሙከራ ትግበራ ለማድረግ የዝግጅት ስራዎች እየተከናወነ ነው

አዲስ አበባ፣ ህዳር 16፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የኤሌክትሪክ አውቶብስ የሙከራ ትግበራ ለማድረግ የዝግጅት ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸው ተገልጿል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ የፋይናንስ እና የቴክኒካል ድጋፍ ለማግኘት ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራ ይገኛል።

በዚህም የኤሌክትሪክ አውቶብስ በከተማው ላይ የሙከራ ትግበራ ለማከናወን ተቀማጭነቱ ለንደን ካደረገው ሲ40 ሲቲስ ጋር በቅንጅት በመስራት ላይ ይገኛል ተብሏል።

ቢሮው ከሲ40 ሲቲስ ጋር በመተባበርም የኤሌክትሪክ አውቶብስ የሙከራ ትግበራ በከተማዋ ፈጣን አውቶብስ ኮሪደር ላይ እንዴት እንደሚተገበር አለም አቀፋዊ የሁለት ቀናት የቪዲዮ ኮንፈረንስ አውደ ጥናት አካሂዷል።

በአውደ ጥናቱ ላይ ከተለያዩ የመንግስት፣ የግል፣ የምርምር ተቋማት፣ የአውቶቡስ አምራቾች እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የተሳተፉ ሲሆን፤ ተሳታፊዎች በቴክኖሎጂ፣ በፋይናንስ፣ በፖሊሲ፣ በመረጃ አሰባሰብ እና በባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ዙሪያ ውይይት አድርገዋል፡፡

በተጨማሪም ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶችን ለይተው የመፍትሔ አቅጣጫ ያስቀመጡ ሲሆን፤ በፕሮጀክቱ ቀጣይ መረሃ ግብሮች ላይ ምክክር አካሂደዋል፡፡

የአዲስ አበባ መስተዳድር እና የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የተለያዩ የመፍትሄ ሃሳቦችን ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል።

በመሪ እቅዱ ላይ የተቀመጡ የከተማ ፈጣን አውቶብስ ኮሪደሮች የማልማት ስራዎችን በማከናወን ለችግሩ የመፍትሄ አካል የሆኑትን የከተማ ፈጣን አውቶብስ የሚጠቀምባቸውን በናፍጣ የሚሰሩ እና ሌሎቹን አውቶቡሶች በቀጣይ ወደ ኤሌክትሪክ የመቀየር እቅድ አንዱ ነው፡፡

የፕሮጀክቱ ዋና አላማም በአዲስ አበባ የከተማ ፈጣን አውቶብስ እና በሌሎችም የከተማዋ ኮሪደሮች ላይ ባትሪ-ኤሌክትሪክ አውቶቡሶችን /ኢ-ባስ/ በመጠቀም የግሪን-ሀውስ ጋዝ ልቀት ፣ የአየር ብክለት እና የህብረተሰቡን የጤና ችግር መቀነስ ነው።

ከዚህ ባሻገርም ሀገሪቷ ለመለዋወጫ እና ለነዳጅ ምርቶች ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት የምታወጣውን የውጭ ምንዛሬ በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል መባሉን ከአዲስ አበባ ከተማ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል ።

Exit mobile version