Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

መራጮች በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ንቁ ተሳታፊ መሆን አለባቸው- ምሁራን

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 25 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የምርጫ ዋና ተዋናይ የሆኑት መራጮች እያንዳንዱን ሂደት በንቃት መሳተፍ እንዳለባቸው ምሁራን አሳሰቡ፡፡
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ አቶ ከተማው ሙልዬ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ምርጫ ዜጎች በቀጣይ ያስተዳድረናል የሚሉትን ፓርቲ ወይም ግለሰብ የሚመርጡበት ነው ይላሉ፡፡
መራጮች የሚፈልጉትን ፓርቲ ለመምረጥም በሂደቱ ንቁ ተሳታፊ መሆን አለባቸው የሚሉት አቶ ከተማው፣ ይህም ለመምረጥ ህጋዊ መብት የሚሰጣቸውን የመራጮች ካርድ ከመውሰድ ይጀምራል ነው የሚሉት፡፡
በዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሒደት የሚያሸንፈውን የፖለቲካ ፓርቲ የሚወስነው ዜጎች የሚሰጡት ድምጽ ብቻ ነው፡፡
ለዚህም መራጮች ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚቀርቧቸውን የፖሊሲ አማራጮች በደንብ መገንዘብ ይጠበቅባቸዋል፡፡
በማህበራዊ ፣ በኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ዘርፎች የሚቀርቡ አማራጭ ሃሳቦችን ለመመዘንም ንቃተ ህሊናቸውን ማዳበር አለባቸው ይላሉ አቶ ከተማው፡፡
በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ አቶ ይሄነው ምስራቅ በበኩላቸው፥ በቅድመ ምርጫ ዜጎች የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እና ዕጩዎችን ማንነት በደንብ መረዳት እንዳለባቸው ይገልጻሉ፡፡
ፓርቲዎቹ ያቀረቧቸው የፖሊሲ አማራጮች ዜጎችን ምን ያህል ተጠቃሚ ያደርጋሉ የሚለውን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር መፈተሸ ይገባልም ነው የሚሉት፡፡
መራጮች የፓርቲዎችን አማራጭ ሃሳብ ለመረዳት የሚያደርጉት ጥረት ብቻውን በቂ አይደለም የሚሉት አቶ ከተማው፥ ፓርቲወች ያቀረቧቸውን ፖሊሲዎች በተለያዩ አማራጮች በግልጽ ቋንቋ ማስረዳት አለባቸውም ይላሉ፡፡
ከዚህ ባለፈም ምርጫው ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲጠናቀቅ ዜጎች በምርጫው ሂደት በተለያዩ አካላት የሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎች በድጋሚ ማጤን እንዳለባቸውም አውስተዋል፡፡
ምርጫን በተመለከተ የሚወጡ መረጃዎች ሂደቱን በበላይነት ከሚመራው ምርጫ ቦርድ ማጣራት አለባቸው የሚሉት አቶ ይሄነው፥ ከቦርዱ ውጭ የሚሰራጩ መረጃዎችንም ምክንያታዊ ሆኖ መረዳት ይገባል ባይ ናቸው፡፡
እንደ እርሳቸው ገለጻ ይህ መሆኑ ዜጎችን ለግጭት የሚያነሳሱ ሀሰተኛ መረጃዎች እና የጥላቻ ንግግሮችን በቀላሉ ማምከን ያስችላል ነው የሚሉት፡፡
ዜጎች በምርጫ ሂደቱ ከህግ እና መመሪያ ያፈነገጡ ድርጊቶች ሲስተዋሉ ለሚመለከተው አካል ማመልከት እንዳለባቸውም ምሁራኑ አሳስበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version