Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ብልጽግና ፓርቲ ከዓለም አቀፍ የምርጫ የታዛቢዎች ቡድን ጋር ተወያየ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 11፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ብልጽግና ፓርቲ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ የሚካሄደውን ሃገራዊ ምርጫ አስመልክቶ ከዓለም አቀፍ ሪፐብሊካን ተቋም እና ከብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ተቋም የጋራ ዓለም አቀፍ የምርጫ ታዛቢ ቡድን ጋር ተወያየ፡፡
ዛሬ በበይነ መረብ በተደረገው ውይይት የብልፅግና ፓርቲ የህዝብና የውጭ ግንኙነት ኃላፊ ዶክተር ቢቂላ ብልጽግና ፓርቲ ወጥ ሃገራዊ ፓርቲ ሆኖ፥ አካታችና አቃፊ በሆነ መንገድ ራሱን በማደራጀት በአዲስ እሳቤ፣ መዋቅር፣ ፕሮግራምና አሰራር ወደ ስራ መግባቱን ለቡድኑ አባላት አብራርተዋል፡፡
እንዲሁም ፓርቲው ወጣቶች፣ ሴቶችና አካል ጉዳተኞችን ያካተት መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ዶክተር ቢቂላ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የተወሰዱ የሪፎርም እርምጃዎችን ለቡድኑ አባላት ያብራሩ ሲሆን በኢትዮጵያ የተጀመረው የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እንዲሳካና ሁለንተናዊ ብልጽግናዋ እንዲረጋገጥ ፓርቲው አበክሮ እንደሚሰራም አስታውቀዋል፡፡
ፓርቲው ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ሆነ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በመልካም ትብብር በመስራት ላይ እንደሚገኝ ያወሱት ዶክተር ቢቂላ ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የሚጠበቅበትን ሚና በብቃት በመወጣት ላይ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡
የዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ቡድን አባላትም በተሰጠው ማብራሪያ ቅድመ ምርጫውን አስመልክቶ በቂ ግንዛቤ ማግኘታቸውንና ይህም ቀጥሎ ለሚያደርጉት የምርጫ መታዘብ ተልዕኳቸው እንደሚያግዛቸው መግለፃቸውን ከፓርቲው ያገኘነው መረጃ ያመላከታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፦https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version