Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የማዕድን ልማትን ማዘመን ለዘርፉ እድገት ወሳኝ ነው- አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ ፣ግንቦት 10 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በ10 ወራት ውስጥ በወርቅ የወጪ ንግድ ከ553 ሚሊየን ዶላር በላይ  ማግኘት መቻሉን የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ከሁለት አመት በፊት በ2011 ዓ.ም የወርቅ ገበያው በእጅጉ አሽቆልቁሎ 29 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ብቻ የተገኘ ሲሆን÷አሁን ላይ ሚኒስቴሩ በሰራው የለውጥ ስራ ገቢውን በእጅጉ ከፍ ማድረግ መቻሉ ተጠቁሟል።
በ2012 ዓ.ም ከ198ነጥብ 3 ሚሊየን ዶላር የተገኘ ሲሆን÷ በ2013 በ10 ወር ውስጥ 553ሚሊየን ዶላር ተገኝቷል።
በዛሬው እለትም ለዚሁ ውጤት መገኘት ከወርቅ ማውጣት ጀምሮ በሁሉም እንቅስቃሴ ላይ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የምስጋና እና የእውቅና መርሃ ግብር እየተካሄደ ነው።
በመርሃ ግብሩ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ኢንጂነር ታከለ ኡማ፣ በወርቅ ምርት ላይ የተሰማሩና የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
በጉያዋ ወርቅ ተሸክማ የምትኖር እና የተሻለ የማዕድን ክምችት ያላትን ኢትዮጵያ በሚገባ አልተጠቀመችም ሲሉ አቶ ደመቀ መኮንን ገልጸዋል።
በ2012 ከነበረበት የቁልቁለት ጉዞ ወደ ተሻለ ደረጃ በመምጣት የወጪ ምንዛሬ ማስገኘቱን መልካም ውጤት እንደሆነ የገለጹት አቶ ደመቀ ለመጣው ውጤት ባላድርሻ አካላትን አመስግነዋል፡፡
ውስጣዊ አንድነትን እና ህብረትን በማጠናከር የተፈጥሮ ሀብታችንን በሚገባ መጠቀም ይኖርብናልም ነው ያሉት።
በዲፕሎማሲ ስራ እስከ ጥግ ሄደን መልካም ግንኙነትን የምንፈጥር ሲሆን ክብራችን እና ሉአላዊነታችንን ለማንም አሳልፈን አንሰጥም ብለዋል፡፡
የጸጋዋን ያህል ያልተጠቀመችው ኢትዮጵያ የላትን ሀብት በሚገባ ጥቅም ላይ ማዋል ቀጣይ የቤት ስራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ወርቅ በባህላዊ መንገድ መመረት የጀመረ ከ2000 አመታት በፊት እንደነበረ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።
ለወርቅ ምርትና ንግድ ለዚህ መድረስ ባህላዊ አምራቾች ሰፊውን ድርሻ ይይዛሉም ነው የተባለው።
በአሁኑ ወቅት በባህላዊ የወርቅ ምርት ላይ የተሰማሩ ከ1ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ዜጎች ይገኛሉ።
የአመቱ ለውጪ ገበያ ከሚቀርበው የወርቅ ምርት ከ60 በመቶ በላይ ድርሻን የሚይዘው የወርቅ ምርት በባህላዊ መንገድ የሚመረት ነው።
የትግራይ፣ የደቡብ፣ የኦሮሚያ፣ የጋምቤላና ቤንሻንጉል ጉሙዝ በኢትዮጵያ በዚሁ መንገድ ወርቅ በማምረት የሚታወቁ አካባቢዎች መሆናቸው ተመላክቷል።
በሃይማኖት ኢያሱ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version