Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የውጭ ሃይሎች ጫናን በጋራ መከላከል እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶች አሳሰቡ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 13 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ላይ በውጭ ሃይሎች የሚደርሱትን አሉታዊ ጫናዎች በጋራ መከላከል እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶች ገለጹ።
የሃይማኖት አባቶቹ ሕዝቡ ውስጣዊ የፖለቲካና ሌሎች ልዩነቶችን ወደኋላ በማድረግ በአገር ጉዳይ በአንድነት መቆም እንደሚገባ ተናግረዋል።
በተለይም የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ለአገሩ አምባሳደር ሆኖ እንዲሟገት ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ሼህ ቃሲም መሀመድ “ሕዝቡ በአገሩና በብሔራዊ ጥቅሙ ላይ ሊተባበር ይገባል” ያሉ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የውጭ ኃይሎች በሕዳሴ ግድብና በሌሎች ጉዳዮች ላይ የሚያሳድሩትን አሉታዊ ጫና ለማቃለል ሁሉም በጋራ መሥራት እንዳለበትም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን ቤተ-ክርስቲያናት ኅብረት ፕሬዚዳንት ፓስተር ጻድቁ አብዶ በበኩላቸው የውጭ ተጽዕኖን ለማቃለል መፍትሄው በጋራ መቆም ተናግረው”በአገር ውስጥ ሠላምና አንድነት ካለ የውጭ ተጽዕኖ ይቀንሳል፤ በተቃራኒው ሕዝብ ከተከፋፈለና ሠላም ከሌለ ተጽዕኖው ይጨምራል” ብለዋል።
ስለዚህም ሕዝቡ በግድቡም ይሁን በሌሎች ጉዳዮች ብሔራዊ ጥቅምን በሚያስከብር መልኩ በትብብርና በቅንጅት መሥራት እንደሚገባው ማብራራታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ-ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ጠቅላይ ጸሐፊ ቄስ ተሾመ አመኑ የሚሰነዘሩትን ጫናዎች በኅብረት መመከት እንደሚቻል ነው የጠቀሱት።
Exit mobile version