Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ 22 አካባቢ በተፈጠረው ችግር በጠፋው ህይወት የተሰማቸውን ሀዘን ገለፁ

አዲስ አበባ፣ጥር 27፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት 22 አካባቢ በተፈጠረው ችግር በጠፋው የሁለት ሰዎች ህይወት የተሰማቸውን ሀዘን ገለፁ።
 
ጉዳዮችን በውይይትና በሰከነ መንፈስ መፍታት ይቻል ነበር ያሉት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የተፈጠረው ችግር ተገቢ ያልሆነ እና መፈጠር የሌለበት ነው ብለዋል።
 
የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጉዳዩን አጣርተው እንዲያሳውና ወንጀለኞችንም ለህግ እንዲያቀርቡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ጠይቀዋል።
 
የወንጀል ምርመራ የማጣራት ሂደቱን አስመልክቶ ዝርዝር ሪፖርት ለህዝቡ ይፋ እንዲሆን ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
 
እንዲህ ዓይነቱ ክስተት በሚፈጠርበት ጊዜ የግራ ቀኝ ወገኖች በሰከነና በሰለጠነ መንገድ ችግሩን በውይይት መፍታት ሲገባ ወደ ኃይል እርምጃ መገባቱና የሰዎች ሕይወት መጥፋቱ ቤተክርስቲያኒቱን በእጅጉ እንዳሳዘናት ቅዱስ ፓትርያርኩ ገልጸዋል።
 
በመጨረሻም በተፈጠረው ችግር ለሞቱት ወገኖች እረፍተ ነፍስን እንዲሰጥ ፣ ለሟች ቤተ ሰዎችም መጽናናት እንዲያድል በመጸለይ የተፈጠረው ግጭት እንዲረግብና ሰላም እንዲሰፍን ጥሪ አቅርበዋል።
 
በትእግስት ስለሺ
 
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision
Exit mobile version