Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የከተማው አስተዳደር በመሬትና መሬት ነክ ችግሮች ላይ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት መስራቱ ተጠቆመ

በአስተዳደሩ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከተማዋ ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ ለጋዜጠኞች ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳብራሩት፥ በመሬት ወረራ እና ዝርፊያ ላይ የተሰማሩ አካላት ላይ የማያዳግም እርምጃ ለመውሰድ እና በህግ ተጠያቂ ለማድረግ ባለፉት ወራት የማጥራት ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል።

ቀደም ባሉት ዓመታት በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ የሚገኙ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርገውን መመሪያ በመጣስ ህገወጥ የመሬት ወረራ ሲካሄድ እንደነበር በመግለጫው ተመልክቷል።

በከተማዋ ዙሪያ ለከተማዋ አረንጓዴ ልማት እንዲውሉ፥ የተለያዩ እና ለልማት ተነሺ ለሚሆኑ ነዋሪዎች የሚሰጡ ምትክ ቦታዎች ናቸው በህገወጥ መንገድ ለግል ጥቅም ሊውሉ ነበር የተባሉት።

በአዲስ አበባ ከተማ ህገወጥ የመሬት ወረራ፥ በመሬት እና መሬት ነክ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ የሚስተዋለውን የአሰራር ችግሮችን ለመፍታት የከተማዋ አስተዳደር ከባለፈው አንድ ዓመት ወዲህ ስርነቀል ለውውጥ ለማምጣት የተለያዩ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱም ተገልጿል።

ከተፈጸሙት ህገ ወጥ ተግባራት መካከል 497 ይዞታዎች በአርሶ አደሮች ስም በህገወጥ መንገድ ካርታ የወጣባቸው መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን፥ ይህ ችግር በአቃቂ፣ ኮልፌ፣ቦሌ፣የካ እናለሚ ኩራ የክፍለ ከተሞች በስፋት ይታይ እንደነበር አስተዳደሩ እንዲካሄድ ባደረገው የማጣራት ስራ የተገኘ መሆኑ ነው የተገለጸው።

ከዚህ ቀደም ወደ ከተማ አስተዳደሩ የመሬት ባንክ ከገባው 1 ሺህ ሄክታር መሬት፣ 383 ሄክታር መሬት በድጋሚ በግለሰቦች መወረሩ በማጣራት ስራው ማረጋገጥ ተችሏል።

ለአረንጓዴ ልማት ከተለዩ 252 ቦታዎች ውስጥ ደግሞ 35 የሚሆኑ ቦታዎች በግለሰቦች መታጠራቸውና ይህንንም የከተማ አስተዳደሩ በሰራው የማጣራት ስራ ወደ ባንክ እንዱገባ ማድረጉንም ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል።

 

የደረጃው ያሉ የከተማ አስተዳደሩ የመሬት ልማት ማኔጅመንት የቢሮ ኃላፊዎች ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ማድረግን ጨምሮ ዝርዝር ማስረጃዎችን በመንተራስ በፍትህ አካላት በወንጀል እንዲጠየቁ የማድረግ ሂደት መጀመሩንም ገልጸዋል።

ሕገወጥ የመሬት ወረራውን ለመከላከል ኃላፊነታቸውን ባልተወጡ፣ የአርሶ አደሩን መብት ሽፋን በማድረግ መብቱ ለማይገባቸው አካላት የይዞታ ማረጋገጫ የሰጡና መታወቂያ የሰሩ ከክፍለ ከተማ ስራ አስፈፃሚ እስከ ወረዳ ድረስ በሚገኙ አመራሮች ላይ እርምጃው መቀጠሉንም ጠቁመዋል።

በነዚህ ህገወጥ ስራዎች ውስጥ የተሰማሩ አካላት ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ጥቆማና መረጃ በመስጠት ለተባበሩት የከተማዋ ነዋሪዎች ስራ አስኪያጁ ምስጋና አቅርበዋል።

በተያያዘም ለሃይማኖት ተቋማት እና ለሌሎች ማህበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በከተማ ካቢኔ ውሳኔ የተላለፈባቸው 70 ከሚሆኑ ቦታዎች መካከል 39ኙ በውሳኔው መሰረት ያልተላለፉ ሲሆን፥ ከነዚህም ውስጥ 19 የሚሆኑትን ቦታዎች የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አስተዳደር የካቢኔውን ውሳኔ ሳይተገብር መቆየቱ ተገልጿል።

 

በቆንጂት ዘውዴ

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version