Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኢትዮጵያ ለአደጋ ከተጋለጡ ዜጎቿ 70 በመቶውን በራሷ አቅም እየረዳች ነው – ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ለተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋ ከተጋለጡ ዜጎቿ መካከል 70 በመቶ የሚሆንትን በራሷ አቅም እየረዳች መሆኑን የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ገለጸ።

ዓለም ዓቀፍ የአደጋ ስጋት ቅነሳ ቀን ”አብሮነት ለምድራችን ደህንነት” በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ ተከብሯል።

በዕለቱ አደጋ መከላከል ላይ የሚሰሩ የተለያዩ ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነሩ ምትኩ ካሳ እንደተናገሩት÷በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በአየር ንብርት ለውጥ ሳቢያ አደጋዎች እየጨመሩ መጥተዋል።

ኢትዮጵያም በዚሁ ሂደት ውስጥ ለተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋዎች በስፋት ስትዳረግ መቆየቷንና አሁንም መቀጠሉን ኢዜአዘግቧል፡፡

በኢትዮጵያ በ1966 ዓ.ም በሰሜኑ አካባቢ የተከሰተው ድርቅ ወደ ቸነፈር ተቀይሮ 250 ሺህ ሰዎችን መቅጠፉን አቶ ምትኩ አስታውሰዋል።

ከዚህ በኋላም ላለፉት 47 ዓመታት የእርዳታ ማስተባበሪያ መስሪያ ቤት አቋቁማ ዜጎቿን እየታደገች ትገኛለች ነው ያሉት።

በአገር ደረጃ ትልቅ አቅም በመፍጠር ለአደጋ የተጋለጡ ዜጎችን በመንግስት አቅም የማገዝ ስራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን አንስተዋል።
በዚሁ መሰረት 70 በመቶ እርዳታ በመንግስት እየተሸፈነ መሆኑን ጠቅሰው÷ መንግስት ተጨማሪ 1 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ለእርዳታ የሚውል ስንዴ ግዥ እየፈጸመ ይገኛል ብለዋል።

እርዳታ ዘላቂ ጥቅም ስለማያመጣ መንግስት የአደጋ ስጋት ቅነሳ ላይ አተኩሮ የሚሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት ኮሚሽነር ምትኩ።

እስካሁን በተሰራው የአደጋ ስጋት ቅነሳ ስራ እንደ አገር የተሻለ ውጤት መገኘቱን ጠቅሰው÷ በዚሁ ዘርፍ ከተለያዩ ዓለም ዓቀፍ ረጂ ድርጅቶች ጋር በስፋት የሚሰራ ይሆናል ብለዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የዓለም ዓቀፍና አህጉር ዓቀፍ የአደጋ ስጋት ቅነሳ ስራ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች ተወካዮችም መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዓለም ዓቀፍ የአደጋ ስጋት ቅነሳ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ44ኛ ጊዜ፥ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ13ኛ ጊዜ ነው የተከበረው።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version