Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በቀዳማዊት እመቤት ጽ/ቤት በሮጲ ከተማ የተገነባው የኢፋ ሮጲ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ተመረቀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት በሮጲ ከተማ የኢፋ ሮጲ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን አስመረቀ፡፡

ጽህፈት ቤቱ በ2013 ዓ.ም በሁለተኛ ዙር ግንባታቸዉ ከተጀመሩት ትምህርት ቤቶች መካከል የመጀመሪያ የሆነዉን በኦሮሚያ ክልል ምእራብ አርሲ ዞን ሮጲ ከተማ የኢፋ ሮጲ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን ነው ያስመረቀው፡፡

የኢፋ ሮጲ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ በሰባት ወር ጊዜ ዉስጥ የተጠናቀቀ ሲሆን÷ 1ሺህ800 ተማሪዎችን በሁለት ፈረቃ የማስተማር አቅም አለው።

በውስጡም አንድ ቤተመጽሐፍ 18 የመማሪያ 4 የላብራቶሪ ክፍሎች እና የአስተዳደር ህንጻ ያከተተ ነዉ፡፡

ለግንባታዉ 14 ሚሊየን ብር ወጪ እንደተደረገበት ታውቋል፡፡

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፣ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ እና ሌሎች እንግዶችም ተገኝተዋል።

ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ወላጆች እና ወጣቶቹ ለትምህት ቅድሚያ እንዲሰጡ መልዕክትን አስተላልፈው የደብተር፣ ቦርሳና ጫማ ስጦታ ለተማሪዎች አበርክተውላቸዋል።

የቀዳማዊት እመቤት ፅህፈት ቤት ከዚህ ቀደም የልዩ ፍላጎት ትምህርት ቤት እድሳትን ጨምሮ በተለያዩ የሃገሪቱ ከፍሎች 20 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ገንብቶ ማስረከቡ ይታወሳል።

በሁለተኛ ዙር የገነባቸዉን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ማስመረቅ መጀመሩን የገለጸው ጽህፈት ቤቱ የትምህርት ተደራሽነትን ለማገዝ በያዝነዉ አመት የሚጠናቀቁ ሌሎች 7 ትምህርት ቤቶች በመገንባት ላይ መሆናቸውን አስታውቋል።

ፅህፈት ቤቱ በአዲስ አበባ ዲቦራ ፋዉንዴሽን ዉስጥ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ቤትን፣ በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን አበሽጌ ወረዳ፣ በሲዳማ ክልል ኦዲቦኩ ቀበሌ ፣በጅማ ዞን አኮ ወረዳና በምእራብ ሸዋ አምቦ ጎረምቲ ቀበሌና ሌሎች ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን እየገነባ ሲሆን ÷ አርማጪሆ ማሰሮ ደንብ ወረዳ በቅርቡ ግንባታዉ እንደሚጀምር አስታውቋል።

በፍሬህይወት ሰፊው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

Exit mobile version