Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በደህንነትና በጸጥታ ተቋማት ላይ የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነትን በንቃት መከላከል ያስፈልጋል- ኤጀንሲው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በደህንነትና የጸጥታ ተቋማት ላይ የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነትን ለመቀነስ ጥብቅ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ አሳሰበ።
ኤጀንሲው ሁለተኛውን የሳይበር ሳምንት ምክንያት በማድረግ ቁልፍ የሆኑ የመንግስት የጸጥታና ደህንነት ተቋማት የተውጣጡ የአይሲቲና ኮሙንኬሽን ባለሙያዎች ስልጠና እየሰጠ ነው።
የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳሬክተር አንተነህ ተስፋዬ÷ በስልጠናው መክፈቻ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፥ በዓለም ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሳይበር ተጋላጭነት እየጨመረ መጥቷል ብለዋል።
በአውሮፓውያኑ 2020 የወጣ አንድ መረጃ እንደሚያመለክተው÷ ዓለማችን በሳይበር ጥቃት ምክንያት በዚህ ዓመት 2 ነጥብ 5 ትሪሊዮን ዶላር አጥታለች።
የሳይበር ጥቃቱ በዚሁ ከቀጠለ በ2025 ዓለማችን 6 ትሪሊየን ዶላር ሊደርስ የሚችል ገቢ ልታጣ ትችላለች የሚል ግምት መኖሩን ምክትል ዋና ዳሬክተሩ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያም አሰራሮች ወደ ዲጂታል እየተቀየሩ ከመምጣታቸው ጋር ተያይዞ እየተፈጸሙ ያሉ የሳይበር ጥቃቶች እየተበራከቱ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በተለይም የመንግስት የደህንነትና ጸጥታ ተቋማት የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነትን ለመቀነስ ጥብቅ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።
የተቋማቱ ማህበራዊ ትስስር ገፆችና ሌሎች አገልግሎቶች የጥቃት ኢላማ ሊሆኑ ስለሚችሉ ጠንካራ የይለፍ ቃል አጠቃቀምን ጨምሮ ሌሎች ጥንቃቄዎች ያስፈልጋሉ ሲሉ መክረዋል።
የሳይበር ጥቃት የደህንነት መረጃዎችን በመመንተፍ አገርን አደጋ ላይ ስለሚጥል ጥንቃቄውን ማጥበቅ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት፣ ከፌዴራል ፖሊስ፣ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፤ መከላከያና ሌሎች የመንግሥት የጸጥታና የደህንነት ተቋማት የተውጣጡ ባለሙያዎች በስልጠናው ላይ በመሳተፍ ላይ ናቸው ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version