Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ከ574 ሺህ ኩንታል በላይ የአኩሪ አተር ምርት ተሰበሰበ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በምዕራብ ጎንደር ዞን ለፋብሪካ ግብዓትነትና ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ከ574 ሺህ ኩንታል በላይ የአኩሪ አተር ምርት መሰብሰቡን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
ምርቱ የተገኘው በመኸር ወቅት በአኩሪ አተር ከለማው 28 ሺህ 300 ሄክታር መሬት መሆኑን በመምሪያው የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ሞገስ ጋሹ ገልጸዋል፡፡
ከለማው መሬት ውስጥ 10 ሺህ ሄክታር የሚጠጋው በባለሐብቶች የተመረተ መሆኑን የተናገሩት ባለሙያው÷ ቀሪው በአርሶ አደር ደረጃ የተሸፈነ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በአኩሪ አተር ልማቱ ከ11 ሺህ 400 የሚበልጡ አርሶ አደሮችና ባለሐብቶች የተሳተፉ ሲሆን÷ 206 የሚሆኑት ደግሞ በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ ባለሐብቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።
የተሰበሰበውን የአኩሪ አተር ምርት አምሥት ባለሐብቶችና ሰባት ድርጅቶች ለፋብሪካ ግብዓትነትና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ግዥ እየፈፀሙ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በዞኑ ባለፈው ዓመት በ8 ሺህ ሄክታር መሬት በአኩሪ አተር ለምቶ ከ14 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን የጠቆሙት አቶ ሞገስ ጋሹ ÷ ከአኩሪ አተር የሚገኘው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በመጨመሩ የሚለማው መሬትና የሚሰበሰበው ምርት እድገት እያሳየ ነው ብለዋል፡፡
በዞኑ ለአኩሪ አተር ልማት ምቹ የሆነ ከ100 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመኖሩ አርሶ አደሩንና ባለሐብቱን በስፋት በማሳተፍ ምርቱን ለማሳደግ እንደሚሰራ ገልጸው ÷ ከአኩሪ አተር መፈልፈያ ማሽን እጥረት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት ማሽኑን ለማቅረብ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version