Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ሚኒስቴሩ በ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ በቤት ልማት ስራ 4 ነጥብ 4 ሚሊየን ቤቶችን ለመገንባት ማቀዱን ገለጸ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 25 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ በቤት ልማት ስራ በከተማ ቤት ልማት ንዑስ ፕሮግራም 4 ነጥብ 4 ሚሊየን ቤቶችን ለመገንባት መታቀዱን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር አስታውቋል።
 
ከዚህ ባለፈም በገጠር የቤት ልማት ንዑስ ፕሮግራም 2 ነጥብ 8 ሚሊየን የሚደርሱ ቤቶችን ለመገንባት ዕቅድ መያዙ ተመላክቷል፡፡
 
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ ወደ ትግበራ ምዕራፍ ለማሸጋገር በዛሬው ዕለት አገር አቀፍ ጉባኤ እየተካሄደ ነው።
 
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ÷አሁን ላይ ቀደም ሲል በስራ ላይ የነበሩት የከተማ ቤት አቅርቦት የስትራቴጂ ማዕቀፍና የገጠር ቤት ልማት ስትራቴጂ የተሻለ አቅም በሚፈጥርና የግል ሴክተሩን ተሳትፎ በሚያጎለብት መልኩ “የቤት ልማት ስትራቴጂ” በሚል በአንድ ሰነድ ተጠቃልሎ መዘጋጀቱን አስታውሰዋል፡፡
 
በዚህም በኢትዮጵያ ከተሞች ተደራሽና ተመጣጣኝ የመኖሪያ ቤቶችን በፍጥነት፣ በጥራትና በብዛት ለማቅረብ በሂደትም ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ለማጎልበት ብሎም ያረጁና የተፋፈጉ የከተማ አካባቢዎችን ለማደስ በሚያስችልና የግል ዘርፉን በስፋት በሚያሳትፍ መልኩ የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል፡፡
 
ካለፉት ዓመታት የልማት ውጤቶችና ልምድ በመነሳት በአገረቱ በመኖሪያ ቤት ልማትና አስተዳደር ዘርፍ መዋቅራዊ ለውጥ በማድረግ በቤት ልማት ዘርፍ የግል ሴክተሩ የአንበሳውን ድርሻ እንዲወስድ የሚያስችል ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል ሚኒስትሯ፡፡
 
በሚቀጥሉት አስር ዓመታጽም በከተሞች ለመገንባታ ከተያዘው 4 ነጥብ 4 ሚሊየን ቤት ውስጥ የግል ሴክተሩ 80 በመቶውን ይሸፍናል ተብሎ በዕቅድ መቀመጡን አመላክተዋል።
 
በዚህም የግል ባለሃብቶች በመኖሪያ ቤቶች ልማት ውስጥ የሚኖራቸውን ተሳትፎ ትርጉም ባለው መልኩ በከፍተኛ መጠን ለማሳደግ መታቀዱንአስረድተዋል፡፡
 
ከእቅዱ ጋር ተያይዞም በመካከለኛ እና ከፍተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለመፍታት የሚያስችሉ አቅሞችና ዕድሎችን በሚገባ በመፈተሽ፣ በማገዝና በመደገፍም ጭምር ያለውን የአቅርቦት ችግር ለመፍታት መንግስት ገና ከመነሻውም ተግዳሮት ያላጣውን የሪል ስቴት ዘርፍ ችግሮች በውል ለመፍታት እየሰራ እንደሚገኝም አብራርተዋል፡፡
 
የሪል ስቴት ዘርፉ ተገቢው የህግ ማዕቀፍ እንዲዘጋጅለት በማድረግ እያደገ የሚሄደውን የቤት ፍላጎት አስተማማኝ በሆነ መልኩ ለማስተናገድ እንዲቻል ብሎም የሪል ስቴት አልሚዎች በተገቢው መንገድ እንዲደራጁ በማድረግ ከመንግስት የሚደረግላቸውን ድጋፍ መጠቀም እንዲችሉ ዘርፉን በህግ አግባብ መምራትና የትብብር መንፈስ መፍጠር እንደሚገባም ተመላክቷል፡፡
 
በይስማው አደራው
Exit mobile version