Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የቡሬ የተቀናጀ ግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ የተግባር ማስጀመሪያ መርሐ-ግብር ተካሄደ

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በ8 ቢሊየን ብር ወጪ የተገነባው የቡሬ የተቀናጀ ግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ የተግባር ማስጀመሪያ መርሐ- ግብር በባሕርዳር ተካሄደ ።

ፓርኩ የክልሉን አርሶ አደር ሸክም በማቅለል ሚናው ላቅ ያለ መሆኑ ተነግሯል፡፡

በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ እና የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበልን ጨምሮ ከፍተኛ የፌደራልና የክልል የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በመርሐ ግብሩ በክልሉ የሚገኙ የግብርና ምርት አቅራቢዎችና ማኅበራት ምርቶቻቸውን አሳይተዋል።

በአማራ ኢንዱስትሪ ልማት ኮርፖሬሽን አዘጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው መርሐ- ግብር የክልሉ የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊው አቶ እንድሪስ አብዱ፥ የኢንዱስትሪ ፓርኩ የግብርና ውጤቶችን ዕሴት ጨምሮ ወደ ውጭ ገበያ ለመላክ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ክልሉ በጦርነት ውስጥም ሆኖ የልማት ተግባራትን በሌላ በኩል እያካሄደ የልማት ተምሳሌት በመሆኑ ምስጋና ይገባዋል ብለዋል።

አሁን ዋና ትኩረታችን ድህነትን ማሸነፍ ነው ያሉት ሚኒስትሩ በዚህ ጥንካሬ በጋራ መስራት ከቻልን በአጭር ጊዜ ለውጥና ዕድገትን ማስመዝገብ ይቻላልም ነው ያሉት፡፡

በክልሉ የቡሬ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጨምሮ በደብረ ብርሃንና ኮምቦልቻ የሚገኙት ፓርኮች በክልሉ ለሚገኙ አርሶ አደሮችና ወጣቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር ግብርናውን በማዘመን የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማሳደግም ጉልህ ሚና እንደሚጫወቱም ነው የተናገሩት።

ከሀይል አቅርቦት ጋር በተያያዘ የነበረበትን ችግር ለመቅረፍም መንግስት አስፈላጊ ግብአቶችን ከውጪ በማስመጣት በቅርቡ ስራ ለማስጀመር መዘጋጀቱን ገልፀዋል።

በሙሉጌታ ደሴ

Exit mobile version