Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት ጠቅላላ ስብሰባ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 25 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)24ኛው የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት ጠቅላላ ስብሰባ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

የህብረቱ ስብሰባም ከዛሬ ጀምሮ እስከ ህዳር 30 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ እንደሚቀጥል ተገልጿል።

ስብሰባው በሽብር ወንጀል፣ በሕገ-ወጥ የሰዎችና የጦር መሳሪያ ዝውውር፣ በአደንዛዥ ዕፅ፣ በእንስሳት ዘረፋ እና በሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ላይ እንደሚመክር ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል ዘለላም መንግስቴ፤ የህብረቱ የስራ ኃላፊዎች፣ የቀጣናው ኢንተርፖል ኃላፊዎች፣ አታሼዎች፣ የየአገራቱ የፖሊስ አዛዦች በስብሰባው እየተሳተፉ እንደሚገኙ ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ኢትዮጵያም የህብረቱን ስብሰባ ስታዘጋጅ የዘንድሮው ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን÷ ከዚህ ቀደም በ2008 ዓ.ም ስብሰባውን ማስተናገዷ ይታወቃል።

14 አገራትን በአባልነት ያቀፈውና ተቀማጭነቱን በኬኒያ ናይሮቢ ያደረገው ህብረቱ በምስራቅ አፍሪካ አገራት የሕግ አስከባሪ ተቋማትን ትብብር ለማጠናከር፣ መረጃ ልውውጥ ለማጎልበት፣ የጋራ ስትራቲጂ ለመንደፍ እና በቀጣናው ሰላም ለማስፈን የሚሰራ መሆኑ ተመላክቷል።

Exit mobile version