Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በደቡብ ክልል የኮሮና በሽታ ወረርሽኝን ለመከላከል የህዝብ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲቋረጥ ተወሰነ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 21 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ)በደቡብ ክልል ከዛሬ ከቀኑ 6 ሰዓት ጀምሮ አዲስ አበባን ጨምሮ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች ወደ ወደ ደቡብ ክልል ሁሉም የህዝብ የትራንስፖርት አገልግሎት ስምሪት እንዲቋረጥ ተወሰነ፡፡

የደቡብ ክልል የኮሮና ወረርሽኝ በሽታ መቆጣጠሪያና መከላከል ግብረ ሀይል ዛሬ በሰጠው መግለጫ ከፍተኛ አገር አቋራጭ ትራንስፖርትና ከክልል ወደ ክልል የሚደረግ አነስተኛና መለስተኛ የህዝብ ትራንስፖርት ስምሪት ላልተወሰነ ጊዜ መቋረጡን ገልጿል፡፡

ክልሉን አቋርጠው የሚያልፉ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት በክልሉ ወሰን ውስጥ ተሳፋሪን ሳያራግፉና ሳይጭኑ በተፈቀደላቸው ስምሪት ብቻ ማለፍ ይችላሉ።

በክልሉ ባሉት ዞኖች መካከልና ከዞን ወደ ወረዳ የሚኖሩ ማናቸውም የህዝብ ትራንስፖርት ስምሪት ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቋረጥ ውሳኔ ተላልፏል ነው የተባለው፡፡

በክልሉ በየትኛውም አካባቢ በባለ ሁለት እግር ሞተር ሳይክል የሚደረግ እንቅስቃሴ ለመንግስታዊ ስራና ለግል አገልግሎት ውጪ ብቻ የተፈቀደላቸው ሲሆን የትራስፖርት አገልግሎት መስጠት እንደማይቻሉ ግብረ ሀይሉ አስታውቋል።

ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ወደ ቤተሰቦቻቸው የሚመለሱ ተማሪዎችን የሚያመላልሱ የትራንስፖርት አገልግሎቶች በልዩ ሁኔታ የሚስተናገዱ ይሆናል ተብሏል።

የከተማ ታክሲን በተመለከተ 12 ሰዎችን የመጫን አቅም ያላቸው ተሸከርካሪዎች 6 ሰዎችን እንዲጭኑ ውሳኔ ተላልፏል፡፡

ባለ 3 እግር ባጃጅ 2 ሰዎችን ጭነው አገልግሎት እንዲሰጡ የተወሰነ ሲሆን የመጫን ልካቸው 8 የሆነ ተሸከርካሪዎች 5 ሰዎችን ብቻ መጫን እንዲችሉ መወሰኑን ግብረ ሀይሉ በሰጠው መግለጫ ተመላክቷል፡፡

ግብረ ሀይሉ ውሳኔውን ተግባራዊ ለማድረግ የክልሉ ህዝብ ለተግባራዊነቱ እንዲተባበር ጥሪ ማቅረቡን ከክልሉ ኮሙኒኬሽ ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

Exit mobile version