አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግስታት የስነ ህዝብ ድጋፍ (ዩኤንኤፍፒኤ) የሴቶችን ጥቃት ለመከላከል እና በስነ ተዋልዶ ተጋላጭ የሆኑ ሴቶችን ጫና ከመቀነስ አንፃር ከመንግስት ጋር እየሰራ መሆኑን ገለጸ፡፡
ዩኤንኤፍፒኤ ፥ በኢትዮጵያ 50ኛ ዓመቱን ባከበረበት ወቅት የኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስትር ዲዔታ ሰመሪታ ሰዋሰውና የድርጅቱ የምስራቅ አፍሪካ እና ደቡብ አፍሪካ ዳይሬክተር ሊድያ ዚጎሞ ተገኝተዋል።
ወይዘሮ ሰመሪታ ሰዋሰው÷ ድርጅቱ በኢትዮጵያ ላይ እያከናወናቸው ያሉትን ተግባራት በማድነቅ በቀጣይነት መንግስት አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርግ ገልፀዋል።
የምስራቅ አፍሪካ እና ደቡብ አፍሪካ ዳይሬክተር ሊድያ ዚጎሞ በበኩላቸው ÷ ድርጅቱ በኢትዮጵያ የሴቶችን ጥቃት በመከላከል፣ የእናቶችን ሞት በመቀነስ፣ ያለአቻ ጋብቻን በማስቀረት ረገድ አበረታች ውጤት ማስመዝገቡን ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግስታት የስነ ህዝብ ድጋፍ ፥ በፈረንጆቹ 1973 በመመስረት በስነ ተዋልዶ፣ በቤተሰብ ምጣኔ፣ በእናቶች ጤና እንክብካቤ፣ ፆታን መሰረት ያደረገ ጥቃትን በመከላከል ላይ የሚሰራ የተራድኦ ተቋም ነው።
በታሪኩ ወ/ሰንበት