Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ተመድ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ በግድቡ ዙሪያ ያለቸውን ልዩነት በውይይት እንዲፈቱት አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያለቸውን ልዩነት በጋራ ውይይት እንዲፈቱት አሳሰበ።

በግብፅ በግድቡ ዙሪያ እየተደረገ ያለው ድርድር ከስምምነት ላይ ሳይደረስ የውሃ ሙሌት እንዳይጀመር ስትል ለተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ደብዳቤ ማስገባቷ ይታወሳል።

ሀገሪቱ የፀጥታው ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ መክሮ የውሳኔ ሀሳብ ያሳልፋል ብላ ብትጠብቅም፤ የዲፕሎማቲክ ምንጮች እንዳስታወቁት ግን ምክር ቤቱ በጉዳዩ ላይ ምንም አይነት ስብሰባ እንደማያደርግ እና የውሳኔ ሀሳብ እንደማያሳልፍ አረጋግጠዋል።

ይልቁንም ሀገራቱ ልዩነታቸውን በጋራ እንዲፈቱ በደብዳቤ ብቻ እንደሚያሳውቅም ዲፕሎማቲክ ምንጮቹ አስታውቀዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አስመልክቶ ግብፅ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ጥያቄ ማቅረቧን ተከትሎ ኢትዮጵያ ያላትን አቋም በድጋሚ ለምክር ቤቱ ግልጽ አድርጋለች።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ለፀጥታው ምክር ቤት በላኩት ደብዳቤም፥ ኢትዮጵያ እየገነባች ያለችው ግድብ የታችኛውን የተፋሰስ አገር እንደማይጎዳ እና የሰላም እና ፀጥታ ስጋትም አለመሆኑን በድጋሜ አረጋግጠዋል።

ሱዳንም፤ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ በድርድር ሂደት ላይ እያለ ግብፅ ጉዳዩን ወደ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት መውሰዷን እንደማትቀበል መግለጿ ይታወቃል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፋን ጃሪክም በእለታዊ መግለጫቸው ህዳሴ ግብድን አስመልክቶ ለኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ መልእክት አስተላልፈዋል።

ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው፥ ሶስቱ ሀገራት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያለቸውን ልዩነት በጋራ በመምከር መፍታት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ሀገራቱ በአውሮፓውያኑ በ2015 በግድቡ ዙሪያ በፈረሙት የመርሆዎች ስምምነትን በመከተል ለልዩነቶቻቸው መፍትሄ ማበጀት ይገባቸዋል ሲሉም አሳስበዋል።

ምንጭ፦ cgtn.com

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

Exit mobile version