Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፈቂ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 10፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፈቂ ማህማት ጋር ተወያዩ።

በውይይታቸው በአፍሪካ ህብረት 33ኛው የመሪዎች ጉባኤ ቅድመ ዝግጅት፣ በአካባቢያዊ የፖለቲካና የጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ለ33ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ አስፈላጊውን የቅድመ ዝግጅት ስራ የሚሰራና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ የሚመራ አዘጋጅ ብሄራዊ ኮሚቴ በማቋቋም የዝግጅት ስራ መጀመሩን አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ አስተናጋጅ ሀገር እንደመሆኗ ጉባኤው የተዋጣለት እንዲሆን ከዚህ ቀደም ከተካሄዱት ጉባኤዎች በተሻለ መልኩ ለማካሄድ መንግስት ፍላጎት እንዳለው ተናግረዋል።

ለጉባኤው ውጤታማነትም መንግስት ከአፍሪካ ህብረት ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ዝግጁ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፈቂ በበኩላቸው ባለፉት አመታት በኢትዮጵያ የተካሄዱ የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ የመስተንግዶ ዝግጅቶች ውጤታማ እንደነበሩ አስታውሰዋል።

የዚህ ዓመት የአፍሪካ ህብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና የመሪዎች ጉባኤ ጭብጥ “ሰላም” እንደመሆኑ የዘንድሮው የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሽልማቱ የእርሳቸው ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ኩራት መሆኑን ገልጸዋል።

ለጉባኤው መሳካትም በጋራ ለመስራት ዝግጁ እንደሆኑ መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የዘንድሮው የአፍሪካ ህብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና የመሪዎች ጉባኤ ከጥር 28 እስከ የካቲት 2 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

Exit mobile version