Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

6ኛው ሃገር አቀፍ ምርጫ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 14 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን 6ኛ ሀገራዊ ምርጫ አስመልክቶ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎችን ሰርተዋል፡፡

የብሪታንያ ቢቢሲ በዓለም አቀፍ ዘገባ አምዱ ላይ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ የመጀመሪያውን ምርጫ እያካሄዱ እንደሆነ ገልጿል፡፡

በኮቪድ19 ምክንያት ከተያዘለት ቀን ዘግይቶ የተካሄደው ምርጫ ግጭት ካለበት የትግራይ ክልል ውጭ ባሉ የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተካሄደ ስለመሆኑም ነው የገለጸው፡፡

ዩሮ ኒውስ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግስት የመጀመሪያ ባለው ነጻ ምርጫ ላይ ኢትዮያውያን እየመረጡ ነው ብሏል፡፡
በአፍሪካ በሕዝብ ብዛት ሁለተኛ ችኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ሀገር አቀፍ እና የክልል ምርጫ ላይ መራጮች ከምርጫው ሰዓት አስቀድመው መገኘታቸውን ዘገባው አስነብቧል፡፡

የምርጫው ውጤትም ከኢትዮጵያ አልፎ በመላው ዓለም የሚያስተጋባ ምርጫ ነው ብሎታል፡፡
ሲ ጂ ቲ ኤን ደግሞ የምርጫ ቦርድ ፍትሃዊ ምርጫ ለማካሄድ በገባው ቃል መሠረት ኢትዮጵያውያን መምረጥ ጀምረዋል በሚል በፊት ገጹ ላይ አስነብቧል፡፡
ከ37 ሚሊየን በላይ ሰዎች ይሳተፉበታል በተባለው ምርጫ ላይ ድምጽ ለመስጠት ገና በማለዳው የወጡ ሰዎች የፈጠሯቸው ረጃጅም ሠልፎች በመዲናዋ አዲስ አበባ መታየታቸውንም በምስል አስደግፎ ይዞ ወጥቷል፡፡

አስመራጮችን ለመመልመል እና ለማሰልጠን እንዲሁም የምርጫ ወረቀቶችን ለማሳተምና ለማሰራጨት በተፈጠረው መዘግየት ቀኑ የተራዘመው 6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ በዛሬው ዕለት እየተካሄደ ነው በሏል፡፡

በጠቅላላ ከ40 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከ9 ሺህ 500 በላይ እጩዎች እንደሚሳተፉ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version