Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በምግብ ምርት ራስን ለመቻል በተካሄደው ሁለገብ ጥረት ውጤት ተመዝግቧል – ግብርና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በምግብ ምርት ራስን ለመቻል በተደረገው ሁለገብ ጥረት በ2013 በጀት ዓመት የዋና ዋና ሰብሎች የመኸር ምርት ወደ 342 ሚሊየን ኩንታል ከፍ ማለቱን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ጠቁሟል።
በአነስተኛ ይዞታ የሚመረተው የዋና ዋና ሰብሎች የመኸር ምርት በ2003 በጀት ዓመት ከነበረበት 222 ሚሊየን ኩንታል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ወደ 342 ሚሊየን ኩንታል ለማደግ ችሏል።
ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ እንደሚያብራራው በአነስተኛ ይዞታ የሚመረተው የአትክልትና ፍራፍሬ የመኸር ምርት በ2003 በጀት ዓመት ከነበረበት 22 ሚሊየን ኩንታል በ2013 በጀት ዓመት 60 ሚሊየን ኩንታል ደርሷል።
የኢትዮጵያ የግብርና አጠቃላይ ሀገራዊ ምርት ዕድገት ከ2003 እስከ 2012 በጀት ዓመት 8 በመቶ አማካይ ዕድገት ለማስመዝገብ ታቅዶ በየዓመቱ የ5 ነጥብ 3 ዕድገት ማስመዝገቡንም ነው መረጃው የሚጠቁመው።
በአማካይ በየዓመቱ የሰብል ምርት 6 ነጥብ 1 በመቶ እንዲሁም የእንስሳት ሀብት 3 ነጥብ 7 በመቶ አድጓል። በተመሳሳይ የደን ንዑስ ዘርፍ በአማካይ በየዓመቱ 3 ነጥብ 4 በመቶ ዕድገት አሳይቷል።
በዘርፉ የተመዘገበው አጠቃላይ ሀገራዊ የምርት ዕድገት ከሕዝብ ዕድገት ምጣኔ በላይ በመሆኑ ለገጠር ድህነት ቅነሣ አስተዋጽኦ ከማድረጉም ባሻገር በምግብ ራሳችንን እንድንችል ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም መረጃው አመላክቷል፡፡
ይህ የምርት ዕድገት የተመዘገበው በንዑስ ዘርፉ በታየው የምርታማነት ዕድገት በተለይም በአትክልት ከ629 በመቶ በላይ፣ በስራስር ከ100 በመቶ በላይ፣ በፍራፍሬ 9 በመቶ አማካይ የምርታማነት ጭማሪ በመመዝግቡ እንደሆነ ጠቁሟል።
ዘርፉን በዘላቄታዊ ለማሸጋገር እንዲሁም የኢትዮጵያን የብልፅግና ጉዞ ከግብ ለማድረስ ቀደም ሲል የነበረው የግብርናና የገጠር ልማት ፖሊሲ ተሻሽሎ እንዲጸድቅ ለሚመለከተው አካል መቅረቡንም መረጃው አስታውቋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version