Fana: At a Speed of Life!

በእስራኤል የበይነ መረብ የቡና ማስተዋወቂያ መድረክ ተዘጋጀ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 21፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በእስራኤል የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከእስራኤል የንግድ ምክር ቤቶች ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር የቡና ማስተዋወቂያ መድረክ አካሄደ።
በመድረኩ በኢትዮጵያ እና በእስራኤል በቡና ዘርፍ የተሰማሩ የንግድ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ተሳትፈዋል።

ኢምባሲው ይህን አይነት አውደ ርዕይ እና ቢዝነስ ፎረም ሲያዘጋጅ ሦስተኛ ጊዜው ሲሆን፣ በበይነ መረብ ሲያካሂድ የመጀመሪያው መሆኑም ነው የተገለጸው።

በእስራኤል የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር እና ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ረታ ዓለሙ በመንግስት በኩል የንግድ ትብብሩን ለማጠናከር ያለውን ቁርጠኛ አቋም በመጥቀስ፥ እስራኤላውያን የኢትዮጵያን ቡና እንዲያገኙ ኤምባሲው የተቻለውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን የገበያ ልማት እና ፕሮሞሽን ዳይሬክተር አቶ ታጠቅ ግርማ ኢትዮጵያ የቡና መገኛ መሆኗን ጠቅሰው፥ የኢትዮጵያን ቡና ዝርያ ልዩ መሆኑን፣ በኢትዮጵያ ካሉት የቡና አይነቶች 37 መለየታቸውን፣ ከእነዚህ መካከል የይርጋጨፌ፣ የሐረር፣ ሲዳማ፣ ሊሙ፣ ጅማ እና ነቀምት ዋና ዋና መሆናቸውን አስታውቀዋል።

በስብስባው የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር፣ የኢትዮጵያ ቡና ቆይዎች ማህበር፣ የኢትዮጵያ ቡና አልሚዎች ማህበር፣ የውመን ኤንድ ኮፊ አባላት መሳተፋቸውን በእስራኤል የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.