የሚኒስትሮች ምክር ቤት የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳለፈ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 31ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
ምክር ቤቱ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል፡-
1. ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው የወጪ ንግድ የቀረጥ ማበረታቻ ሥርዓት አዋጅን ለማሻሻል የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡ ለኢንደስትሪ ልማትና ኢንቨስትመንት የሚያስፈልገውን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ለማሳደግ፣ በወጪ ንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች በማበረታታት ረገድ የታዩ ውስንነቶችን ለመቅረፍ እና የዘርፉን ተዋንያን የሚያበረታታ ሥርዓት በመዘርጋት ተወዳዳሪነት ማላቅ ይቻል ዘንድ ረቂቅ ማሻሻያ አዋጅ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም ረቂቅ ማሻሻያ አዋጁ ላይ ከተወያያ በኋላ ግብዓቶችን በማከል ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
2. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው የፌዴራል ህብረት ስራ ኮሚሽን ለሚሰጣቸው አገልግሎቶች የሚያስከፍለውን የአገልግሎት ክፍያ ለመወሰን በቀረበ ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡ ኮሚሽኑ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ማስፋት፣ የአገልግሎቶቹን የጥራት ደረጃ ማሻሻል፣ ብሎም የተጠቃሚውን ማህበረሰብ አቅም ባገናዘበ መልኩ አገልግሎት ለመስጠት ያወጣውን ወጪ በከፊል መሸፈን የሚያስችል ስርዓት መዘርጋት በማስፈለጉ ረቂቅ ደንቡ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቡ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
3. ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየው የጤና ፖሊሲ ላይ ነው፡፡ በስራ ላይ ያለው የጤና ፖሊሲ ላለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ማሻሻያ ሳይደረግበት መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ፖሊሲው በጸደቀበት ወቅት ከነበረው ጠቅላላ የህዝብ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ፣ እየተከሰቱ ያሉ ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መበራከት፣ በሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ደረጃ በጤና ዙሪያ የሚከሰቱ ለውጦች፤ዘርፉ ጥራት እና ፍትሀዊነት ያለው አገልግሎት ከመስጠት አኳያ ችግሮች የሚስተዋሉበት በመሆኑ እንዲሁም ከሀገራችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ጋር የሚጣጣም የጤና ፖሊሲ እንዲኖረን አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ረቂቅ ፖሊሲው ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ ፖሊሲው ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል ከጸደቀበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
4. በመጨረሻም ምክር ቤቱ የተወያየው በግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ ላይ ነው፡፡ በስራ ላይ የነበረው የግብርና ፖሊሲ ከአዳጊ የምርትና ምርታማነት ፍላጎት ጋር አብሮ መጓዝ የቻለ ባለመሆኑ፤ ለግብርናው ዘርፍ እድገት ማነቆ የሆኑ አሰራሮችን መለወጥ አስፈላጊ በመሆኑ እንዲሁም ሀገራችን ከምትከተለው ብዝሀ ዘርፍ የኢኮኖሚ ስርአት ጋር የሚጣጣም ፖሊሲ ማስፈለጉ ታምኖበታል፡፡ ስለሆነም የግብርና ዘርፍን ከሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች ጋር የበለጠ የሚያስተሳስር፣ የተፈጥሮ ሃብትን መጠበቅና በዘላቂነት መጠቀም የሚያስችል፤ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንዲሁም በገጠር መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት የሚያግዝ ረቂቅ ፖሊሲ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡
ምክር ቤቱም በረቂቅ ፖሊሲው ላይ ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል ከጸደቀበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡