Fana: At a Speed of Life!

ከስጋና ወተት ምርት 68 ሚሊየን ዶላር ገቢ ተገኘ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 11 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በ2012 በጀት ዓመት 11 ወራት ውስጥ ወደ ውጪ ከተላከ የስጋና ወተት ምርት 68 ነጥብ 13 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱን ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒቴር አስታወቀ።
 
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የስጋና ወተት ኢንስቲትዩት የ2012 በጀት ዓመት የ11 ወራት የወጪ ንግድ አፈፃፀምን በዘርፉ ከተሰማሩ ባለድርሻ አካላት ጋር ገምግሟል።
 
በዚህም በበጀት ዓመቱ 11 ወራት ከስጋና ወተት 113 ነጥብ 81 ሚሊየን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ 68 ነጥብ 13 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ የተገኘ ሲሆን÷ ከበግና ፍየል ስጋ 61 ነጥብ 31 ሚሊዮን ዶላር፣ ከዳልጋ ከብት 1 ነጥብ 3 ሚሊየን ዶላር፣ ከእንስሳት ተረፈ ምርት 2 ነጥብ 93 ሚሊየን ዶላር እንዲሁም ከማር፣ ከሰም፣ ከዓሳ ምርት እና ከወተት 2 ነጥብ 60 ሚሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱ ተገልጿል።
 
የስጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲቱት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን ጋሹ÷ የእርድ እንስሳት አቅርቦት ጥራት ችግር፣ የእንስሳት ማቆያ እጥረት፣ የብድር አቅርቦት እጥረት፣ ህገ-ወጥ የቁም እንስሳት ንግድና የመብራት መቆራረጥ ምክንያት የተያዘውን እቅድ ሙሉ በሙሉ መፈጸም አልተቻለም ሲሉ ተናግረዋል።
 
በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የንግድ ማስፋፊያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ በበኩላቸው÷ ከሚፈለገው አካል ያለመድረስ እንጂ የአቅርቦት ችግር የለም ያሉ ሲሆን በአቅራቢዎችና በቄራዎች መካከል ቀጥተኛ ግንኙነት እንዲኖርና የአቅርቦት ሰንሰለቱን ለማሳጠር እንሰራለን በማለት ተናግረዋል።
 
ዘርፉ አትራፊ ሆኖ አርብቶ አደሩ ተጠቃሚ የሚሆንበት አሰራር በመዘርጋት የወጪ ንግድ ስታንዳርድ ዋጋ በማዘጋጀት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ እንሰራለን ማለታቸውን ከንግድና ኢንዲስትሪ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.