Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል የኢንቨስትመንት ዘርፉን ማስፋፋት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የኢንቨስትመንት ዘርፉን በማስፋፋት ዘላቂ የስራ ዕድል መፍጠር በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ ውይይት እየተካሄደ ነው።

የአማራ ክልል ኢንቨስትመንት እና ኢንዱስትሪ ኮሚሽን ባዘጋጀው በዚህ መድረክ ላይ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች እና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የአማራ ክልል ርዕስ መስተዳድር ልዩ አማካሪ አቶ ጎሹ እንዳላማው፥ በክልሉ የኢንቨስትመንት ዘርፉን በማጠናከር ለዜጎች ዘላቂ የስራ እድል ለመፍጠር ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህም የማሌዥያ ቢግዌን የስራ እድል ፈጠራ ዘዴን በመውሰድ እና የክልሉን ተጨባጭ ሁኔታ መሰረት በማድረግ የስራ እድል ፈጠራ ጥናት መጠናቱን ጠቅሰዋል።

በጥናቱም ለ146 ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል የሚፈጥሩ 34 ቢሊየን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 51 ፕሮጀክቶች መለየታቸውን አብራርተዋል።

ጥናቱ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የሚመራ መሆኑን ያነሱት አቶ ጎሹ፥ በዚህም በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ከመለየት ባለፈ ክትትል እና ቁጥጥር እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

በክትትል እና ቁጥጥር ስራው ሃላፊነታቸውን በማይወጡ የተቋማት ሃላፊዎች እና ባለሙያዎች ላይ ከስራ እስከ ማሰናበት የሚደርስ እርምጃ እንደሚወሰድም ጠቅሰዋል።

የክልሉ የስራ ዕድል ፈጠራ የጥናት ቡድን አስተባባሪ አቶ ሞገስ ተኬ በበኩላቸው፥ ሰብል ልማት፣ እንስሳት ሃብት፣ የወተት ላም ማርባት እና ግብርና ማቀነባበር ለዕቅዱ የተመረጡ የስራ ዘፎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይ በማምረቻው ዘርፍ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም እና በመብራት ሃይል ዘርፎች ላይ እንደሚሰራም አመላክተዋል።

በናትናኤል ጥጋቡ

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.