Fana: At a Speed of Life!

ለዱባይ ኤክስፖ 2020 ዝግጅት የግንባታ ሂደት 10 ሺህ ኢትዮጵያውያን እንዲሳተፉ ከስምምነት ተደረሰ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 7፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የዱባይ 2020 ኤክስፖ በሚካሄድበት ስፍራ እየተደረገ ያለውን ዝግጅት ጎበኙ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ልዑካቸው በዛሬው ዕለት ዱባይ 2020 ለተሰኘው ኤክስፖ እየተከናወኑ ያሉ ዝግጅቶችን ጎብኝተዋል።

በግንባታው ሂደት 10 ሺህ ኢትዮጵያውያን ገብተው እንዲሳተፉም ከስምምነት መደረሱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጉብኝቱ በኋላ ተናግረዋል።

የሰው ልጅ ጭንቅላት ሳይከለከል ከሰራ ያለመውን ማሳካት እንደሚችል ለኤክስፖው እየተደረገ ያለው ዝግጅት ያሳያልም ነው ያሉት።

በዱባዩ 2020 ኤክስፖ ኢትዮጵያ ባህሏንና ምርቷን እንድታስተዋውቅ እንደተፈቀደላትም ይፋ አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ኢትዮጵያ የአፍሪካን ኤክስፖ ለማዘጋጀት ያቀረበችው ፕሮፖዛል በአፍሪካ ህብረት ተቀባይነት ማግኘቱንም አያይዘው ተናግረዋል።

ይህ እንደ አውሮፓውያኑ 2030 ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ይዘጋጃል ተብሎ የታቀደው የአፍሪካ ኤክስፖ በአህጉሪቱ ትልቁ እንደሚሆን ይጠበቃልም ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በነበራቸው ቆይታ ህጋዊ ሰነድ የሌላቸው ዜጎች ያሉባቸው ችግሮች እንዲፈቱ ከስምምነት መደረሱንም በመግለጫቸው አስታውቀዋል።

ከዚህ ባለፈም በሀገሪቱ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ልጆች የሚማሩበት ትምህርት ቤት ለመክፈት ከስምምነት መደረሱን ገለፀዋል።

በዓለም ግዙፉ እንደሚሆን የተነገረው ዱባይ 2020 ኤክስፖ የፊታችን ጥቅምት ወር ላይ የሚከፈት መሆኑ ተገልጿል።

ኤክስፖው ከጥቅምት ወር ጀምሮ ለስድስት ወራት ክፍት ሆኖ እንደሚቆይም ተመላክቷል።

በአልአዛር ታደለ

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.