Fana: At a Speed of Life!

በመላው ዓለም እውቀትና ልምድ ባካበቱ ዳያስፖራዎቻችን ለመጠቀም በሀገር ቤት አመቺ ስርዓት መፍጠር ይገባል ተባለ

አዲስ አበበባ፣ ጥር 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ነጻነቱን አስከብሮ በተጽዕኖው ጠንካራ የሆነ አህጉር ለመፍጠር በምጣኔ ሀብት ለመበልጸግ ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ምሁራን ተናገሩ።

በተለያዩ የአለም ክፍሎች በርካታ እውቀት እና ልምድ ያካበቱ የአፍሪካ ዳያስፖራዎችን በሞያዎቻቸው አገልግሎቶችን መስጠት እንዲችሉ የሚያደርግ አመቺ ስርዓትን መቅረጽ እንደሚገባ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገራቸው እነዚህ ምሁራን አሳስበዋል፡፡

በወጣቶች አህጉርነቷ የምትታወቀው አፍሪካ፣ ድህነትም ሌላኛው መገለጫዋ እንደሆነ መቀጠሉ ከዘርፈ ብዙው ችግሮቿ እንዳትላቀቅ ምክንያት ሆኗታል ይላሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ እና እስያ ጥናት እና ምርምር ማዕከል ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ሳሙኤል ተፈራ።

እንደ እሳቸው ገለፃ ኢትዮጵያ እንኳ ለምሳሌ ብትነሳ ከ70 በመቶው በላይ ህዝቧ ወጣት ነው፡፡

ይሄ ሀይል ምግብ፣ ስራና ማህበራዊ አገልግሎቶችን ይፈልጋል የሚሉት ዶክተር ሳሙኤል፥ መንግስታት ይሄን ማድረግ ካልቻሉ ደግሞ ሌላ የጥፋት ቡድን ይሄንኑ ሀይል ላልተገባ አላማ መጠቀሚያ እንዲያደርገው መፍቀድ እንደሆነ ያስረዳሉ።

በታላቁ “ወደ ሀገር ቤት ኑ” ጥሪ በርካቶች መምጣታቸው የአጭር ጊዜ ስኬት ብቻ እንዳይሆን እና ለዚህ ወጣት ሀይል የስራ እድልን የሚፈጥሩ የኢኮኖሚ አማራጮችን እና አዳዲስ የስራ ሀሳቦችን ይዘው እንዲመጡ ሁኔታዎች ሊመቻቹ ይግባል ባይ ናቸው።

አቶ ጌታሁን አለሙ የኢትዮጵያ ቱሪዝም እና ሆቴል ማርኬት ማህበር ፕሬዝዳንት፥ አሁን ያለውን አፍሪካዊ የመተባበር መንፈስ በማሳደግ ለአህጉራዊ ተጠቃሚነት መስራት ይገባል ይላሉ።

ሀገሩ ነጻ እንድትሆን፣ ከድህነት እንድትወጣ የማይፈልግ ዳያስፖራ የለም የሚሉት አቶ ጌታሁን፥ በሀገር ውስጥ ካለው በተሻለ የገንዘብ፣ የቴክኖሎጂ፣ የእውቀትና የልምድ እድሎች እንደሚኖሩት ያነሳሉ።

ይሄንን እድል ወደዚህ በማምጣት እዚህ ያለውን ሀብት በመጠቀም መስራት ቢቻል፣ መንግስትም ይሄንን የሚመጥን አሰራር ቢዘረጋ አሁን ካለው አህጉራዊ አደረጃጀቶች መጠናከር ጋር ተዳምሮ ብዙ ለውጦችን ማምጣት እንደሚቻል አስረድተዋል።

በተለያዩ የአለም ክፍሎች የሚገኙ የአፍሪካ ዳያስፖራዎች ሙያዊ ክህሎቶቻቸውን በመገልገል አህጉራቸውን የሚጠቅሙበትን ጠንካራ ስልት መቀየስ እንደሚገባም ነው ምሁራኑ የጠቆሙት።

አቶ ጌታሁን ዳያስፖራዎች ጥሪ ሲደረግለት መጥቶ ከመሄድ ውጪ በምን መልኩ አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ ነው የሚለውን ማሰብ እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።

ለአብነትም በትላልቅ የትምህርት ተቋማት እና ሆስፒታሎች የሚሰሩ ዳያስፖራዎች ወደ ሀገር ቤት ሲመጡ በተግባር ሀገራችውን የሚጠቅሙበትን አሰራር መዘርጋት ይቻላል ነው የሚሉት።

በተጽዕኖው የበረታ አህጉር የመፍጠር ጉዞው በምጣኔ ሀብት መጠንከርን ያስቀድመ ሊሆን ስለሚገባው ለመስራት የሚያስችል መደላድል እንዲኖር ተጠይቋል፡፡

ያለውጣውረድ በቀላሉ የኢንቨስትመንት መሬት የሚያገኙበትን፣ ማሽነሪዎችን አስገብተው የሚተክሉበትን፣ ጥሬ እቃዎችን አስገብተው ወደ ማምረት የሚሸጋገሩበትን፣ ከምንም በላይ እውቀትና ልምዳቸውን አምጥተው ለሌሎች የስራ እድል መፍጠር የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት ከተቻለ የዳያስፖራውን ፍሰት መጨመር እንደሚቻል አቶ ጌታሁን ያነሳሉ።

በርናባስ ተስፋዬ

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.