Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የቦሌ ክፍለ ከተማ አብያተ ክርስቲያናት በጦርነት ለተጎዱ ወገኖች የ15 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረጉ

አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አዲስ አበባ አገረ ስብከት የቦሌ ክፍለ ከተማ አብያተ ክርስቲያናት በጦርነት ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች ያሰባሰቡትን የ15 ሚሊየን ብር ዋጋ ያለው ድጋፍ ለክፍለ ከተማው አስተዳደር አስረክበዋል፡፡

በክፍለ ከተማው የሚገኙ ሰባት የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናት ከምዕመናን ያሰባሰቡትን የ15 ሚሊየን ብር ዋጋ ያለው የተለያዩ ቁሳቁሶችን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ እና ጉራጌ አገረ ስብከት ሊቀጳጳስ አቡነ መልከጸዴቅ ለቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ዓለምጸሐይ ሽፈራው አስረክበዋል።

ብጹዕ አቡነ መልከጸዴቅ በርክክቡ ላይ ባደረጉት ንግግር የቦሌ ክፍለ ከተማ አብያተ ክርስቲያናት በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በተካሄደው ጦርነት ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመደገፍ ባደረጉት ከፍተኛ እንቅስቃሴ በአዲስ አበባ ከተማ አገረስብከት በሞዴልነት የሚወሰዱ መሆናቸውን አውስተው፣ ለወገን ደራሽ ለመሆን የመንግሥትን ጥሪ ተቀብለው ላበረከቱት የላቀ አስተዋጽኦ ምስጋና እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡

ድጋፉ ወደፊትም እንደሚቀጥል የገለጹት ብጹዕነታቸው፣ የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደርም በድጋፍ ማሰባሰብ እንቅስቃሴው ላይ ላደረገው መልካም ትብብር ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ድጋፉን የተረከቡት ወ/ሮ ዓለምጸሐይ ሺፈራው በበኩላቸው የቦሌ ክፍለ ከተማ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናት በሕልውና ዘመቻው ወቅት ከፍተኛ ድጋፍ ማበርከታቸውን አውስተው፣ የእምነት ተቋማት ለአገር ሰላም ከመጸለይ ጎን ለጎን የተቸገሩ ወገኖችን ለመደገፍ ምዕመናኑን አስተባብረው የሚያደርጉት ድጋፍ የሚደነቅ መሆኑን በመግለጽ ለተደረገው ድጋፍ በቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ስም ምስጋናቸውን ማቅባቸውን ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የክፍለ ከተማው ቤተክርስቲያናት አስተዳዳሪዎችም ለቀረበው አገራዊ የድጋፍ ጥሪ ምላሽ በመስጠታቸው መደሰታቸውን ገልጸው፣ ወደፊትም አቅማቸው የፈቀደውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ከከንቲባ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.