Fana: At a Speed of Life!

የተፈጥሮ ሃብት ልማትና የመስኖ ስራዎች ኢትዮጵያ ለችግር እንደማትንበረከክ በሚያሳይ አግባብ ይከናወናሉ – አቶ ዑመር ሁሴን

አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ”የዚህ ዓመት የበጋ ወራት የተፈጥሮ ሃብት ልማት የመስኖ ስራዎች ኢትዮጵያ በማንኛውም ችግር የማትንበረከክ መሆኗን ማሳየት በሚያስችል አግባብ ይከናወናሉ” ሲሉ የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን አስታወቁ።

በአማራ ክልል ሰሜን ሜጫ ወራዳ እናምርት ቀበሌ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ ማስጀመሪያና በክረምቱ የተተከሉ ችግኞችን ውሃ የማጠጣት መርሃ ግብር ተካሂዷል።

ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን በወቅቱ እንዳሉት ፥ በኢትዮጵያ በበጋው ወቅት 4 ሚሊየን ሄክታር መሬት የሚሸፍን የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ ለማከናወን ታቅዶ በተለያዩ ክልሎች ተግባራዊ መሆን ጀምሯል።

ከታቀደው መሬት ውስጥ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታሩ በአዲስ የሚለማ መሆኑን ጠቁመው ፥ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታሩ ደግሞ ቀደም ሲል የለማና ለነባር አፈርና ውሀ ጥበቃ ስራዎች የጥገናና ተጓዳኝ ስራዎች የሚከናወንበት መሆኑን አመልክተዋል።

የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራው የአርሶ አደሩን ኑሮ የሚቀይርና የኢኮኖሚ ምንጭ እንዲሆን ታሳቢ ተደርጎ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው ፥ ባለፉት ዓመታት በዘርፉ በተከናወኑ ስራዎች ለውጥ መምጣቱን አመላክተዋል።

“በተለይም በዚህ ዓመት የሚከናወኑ የበጋ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና የመስኖ ልማት ስራዎች እንደ ሀገር ከገጠመን የውስጥና የውጭ ጫና በራሳችን ጥረትና አቅም ለመላቀቅ የሚያስችለን ጠንካራ መሰረት ሊሆን ይግባል” ብለዋል።

“ጠላቶቻችን ‘አይችሉም፤ አይሆንላቸውም’ እያሉ በተለያየ መንገድ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፍላጎታቸውን መሰረት ያደረገ ጫና ለመፍጠር እየሞከሩ ናቸው” ያሉት ሚኒስትሩ ፥ ጫናውን መቋቋም የሚቻለው ጠንክሮ በመስራት ብቻ መሆኑን ነው የጠቆሙት።

የበጋ ልማት ስራውን በቁጭትና በእልህ በማከናወን ኢትዮጰያ በማንኛውም ፈተና የማትንበረከክ መሆኗን በልማት ስራዎቻችን ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልጸው፥ በየአካበቢው ለሚከናወኑ የበጋ ወራት የልማት ስራዎች ሚኒስቴሩ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን በፈጸመው ወረራ በተፋሰሶች ውስጥ የለማ ደን፣ ለተከላ የተዘጋጁ ችግኞች፣ ጥብቅ ደኖችን በማውደም 4 ቢሊየን ብር የሚገመት ሃብት ማውደሙን የገለፁት ደግሞ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ሃላፊ ዶክተር አልማዝ ጊዜው ናቸው።

“በዚህ ዓመት የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራው በሽብር ቡድኑ የወደመውን የተፈጥሮ ሃብት ሊያካክስ በሚችል አግባብና ምርታማነትን ሊያሳድግ በሚችል መልኩ ሆኖ ይከናወናል” ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት የተከናወነው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ አስተዋጽኦ ከማድረጉ ባሻገር የደን ሃብት ሽፋኑን ከ6 ነጥብ 5 በመቶ ወደ 15 በመቶ ማሳደግ ማስቻሉን ጠቅሰዋል።

አርሶ አደሩ በተፋሰሶች ውስጥ በንብ ማነብና በእንስሳት ማድለብ እንዲሁም በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት በመሰማራት የገቢ ምንጩ እንዲሰፋ አስተዋጽኦ ማድረጉንም የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።

በዘንድሮ የበጋ ወቅት ከ4 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ህዝብ በማሳተፍ 8 ሺህ 429 ተፋሰሶችን መሰረት ያደረጉ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች መጀመራቸውን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፤ እንገንባ፤ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.