Fana: At a Speed of Life!

ለሰላም እና እኩልነት አዎንታዊ ሚና ያላቸው ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ እሴቶቻችን ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል-አቶ ቀጀላ መርዳሳ

አዲስ አበባ፣ ጥር 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሰላም እና ለእኩልነት እንዲሁም ለወንድማማችነት አዎንታዊ ሚና ያላቸው ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ እሴቶቻችን ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ሲሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ቀጀላ መርዳሳ ገለጹ፡፡
 
ሚኒስትሩ በአዲስ አበባ ጃንሜዳ የጥምቀት በዓል አከባበር ስነ ስርዓት ላይ ተገኝተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
 
በመልዕክታቸውም አገራችን ኢትዮጵያ እጅግ የሚያኮሩ ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ እሴቶች ያሏት መሆኑን አውስተዋል፡፡
 
እነዚህን ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ ሃብቶችም ለበጎ ነገር ልንጠቀምባቸው ይገባል ነው ያሉት ሚኒስትሩ፡፡
 
በኢትዮጵያ ሃይማኖት ከየትኛው ፖለቲካ አደረጃጀት ነጻ መሆኑን ያስታወሱት ሚኒስትሩ ፥ የሃይማኖት ተቋማትም ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ ሆነው ምዕመናን ማገልገል ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
 
የሃይማኖት አባቶች የነገ አገር ተረካቢ ወጣቶችን በሃይማኖታዊ አስተምህሮ እና በስነ ምግባር በማነጽ የሚጠበቅባቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡
 
ለሰላም እና ለእኩልነት እንዲሁም ለወንድማማችነት አዎንታዊ ሚና ያላቸው ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች፣ ምክክር፣ የሰላም እና የእርቅ ክንዋኔዎች በሁሉም የአገራችን ክፍሎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
 
ዜጎች የጥምቀት በዓልን ሲያከብሩ በጦርነት እና በተለያዩ ምክንያቶች ችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች ድጋፍ እንዲያደርጉም ሚኒስትሩ ጠይቀዋል፡፡
 
 
በቢቂላ ቱፋ፣ አበበ የሸዋልዑል፣ ብርሃኑ በጋሻው እና ገላና ተስፋ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
 
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.