Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ ለሶስት ቀናት የሚቆይ የባህል ፌስቲቫል ከእሁድ ጀምሮ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፣ ጥር 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከፊታችን እሁድ ጀምሮ ለሶሰት ቀናት የሚቆይና 300 ሺህ ሰዎች ይሳተፉበታል ተብሎ የሚጠበቅ የባህል ፌስቲቫል ይካሄዳል።

የአዲስ አበባ ባህል ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳው፤ 13ኛውን ከተማ-አቀፍ የባህል ፌስቲቫል በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል።

የፌስቲቫሉ ዋነኛ ዓላማ የማህበረሰቡን ወግ፣ ባህልና በጎ የሆኑ ማህበራዊ እሴቶችን ማስተዋወቅ መሆኑንም አብራርተዋል።

በሁሉም ክልሎች የሚከወኑ ባህላዊ እሴቶች በመዲናዋ በሚገኙ 11 ክፍለ ከተሞች ለእይታ እንደሚቀርቡ ነው ዶክተር ሂሩት የተናገሩት።

የብሔር ብሔረሰቦች የባህል፣ የእደ ጥበብ ውጤቶች፣ ባህላዊ የግጭት አፈታትና ሌሎች ክዋኔዎች ለህዝብ የሚተዋወቁ መሆኑን ጠቅሰው፥ ፌስቲቫሉ አምራቾችና ሻጮች የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩም የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ባህላዊ ምግብና መጠጦች፣ አልባሳት፥ የዲዛይን ውድድሮችና ሌሎች ሁነቶች ይከናወንበታል ነው ያሉት።

አገር በቀል እውቀቶች እንዳይጠፉ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ተደግፈው ለትውልድ ማስተዋወቅና ማስተላለፍ ስለሚቻልባቸው አማራጮችም የምሁራን ውይይት የሚካሄድ ይሆናል ነው የተባለው።

ከጥር 15 እስከ 17 ቀን 2014 ዓ.ም በጊዮን ሆቴል በሚካሄደው ፌስቲቫል ተሳታፊዎች የአገር ባህል ልብስ ለብሰው መምጣት ይጠበቅባቸዋል ተብሏል።

የመንግስትን ጥሪ ተቀብለው ወደ አገራቸው ለመጡ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት በከተማዋ የተዘጋጁ ባዛርና ፌስቲቫሎች ማጠቃለያ እንዲሆን ሰፊ ዝግጅት መደረጉንም ዶክተር ሂሩት መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.