Fana: At a Speed of Life!

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ከ3 ሺህ 500 በላይ አባወራዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የጤና መድህን አገልግሎት ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በሐረሪ ክልል ከ3 ሺህ 500 በላይ አባወራዎችን ለአንድ ዓመት የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ የሚያደርግ ሁለት ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ፡፡

በድጋፍ ርክክቡ ወቅት የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ኦርዲን በድሪ እንደተናገሩት ÷ በክልሉ የህዝቡን የማኅበራዊና የኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማጎልበት በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፡፡

በማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት የኅብረተሰቡን ጤንነት ለመጠበቅ እየተሠሩ ያሉ ተግባራት አበረታች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ሐረማያ ዩኒቨርሲቲም የማኅበረሰቡን ጤና አገልግሎት ለማሻሻል ከሚሠራቸው ሥራዎች በተጨማሪ በተለያዩ ዘርፎች ድጋፎችን እያደረገ መሆኑንም ጠቁመው ለድጋፉ ምስጋና አቅርበዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና በክልሉ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ቦርድ ሰብሳቢ ሚስራ አብደላ በበኩላቸው ÷ በክልሉ ህዝቡን የማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ተጠቃሚ ከማድረግ አንፃር ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል፡፡

በጤና መድህን አገልግሎት ለአቅመ ደካማ ወገኖች የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ በማድረግ የመደጋገፍ ባሕል እያሳደገ እንደሚገኝም ነው የተናገሩት፡፡

አገልግሎቱ ማህበረሰቡን ከድንገተኛ ወጪ የሚያድን እና የተሻለ የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አክለውም ዩኒቨርሲቲው ያደረገው የ 2 ሚሊየን ብር ድጋፍ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡

ዪኒቨርሲቲው በምስራቁ የኢትዮጵያ ክፍል የሚገኙ የኅብረሰብ ክፍሎችን ተጠቀሚ የሚያደርጉ የተለያዩ ሥራዎች መሥራቱን እንደሚቀጥል የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ጀማል ዩሱፍ ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በቀጣይም በክልሉ በጤና፣ በቱሪዝም፣ በግብርና እንዲሁም በአካባቢ ጥበቃ ዘርፎች ላይ በምርምር የተደገፉ ሥራዎችን ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡

የሀረሪ ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ኢብሳ ሙሳ ÷ የተደረገው ድጋፍ 3 ሺህ 500 በላይ አባወራዎችን ለአንድ ዓመት የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ያመላከተው የሐረሪ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ነው፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.