Fana: At a Speed of Life!

ሁሉም የፌዴራል ጠበቆች በነቂስ ወጥተው በጠበቆች ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሁሉም የፌዴራል ጠበቆች በነቂስ ወጥተው ጥር 15 በሚካሄደው የጠበቆች ጠቅላላ ጉባኤው ላይ በንቃት እንዲሳተፉ የፍትሕ ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ጠበቆች ጠቅላላ ጉባኤን አስመልክቶ የኢፌዴሪ የፍትሕ ሚኒስቴር ማምሻውን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው ጋዜጣዊ መግለጫ፥ ለአገራችን የፍትህ ስርዓትና ለሙያው ዕድገት ብሎም ለሕረተሰቡ የተሻለ የፍትሕ አገልግሎት ለመስጠት የጠበቆች ጠቅላላ ጉባኤ ወሳኝ ሚና ያለው መሆኑን ከግምት በማስገባት ሁሉም የፌዴራል ጠበቆች በነቂስ ወጥተው በጠቅላላ ጉባኤው ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ አስተላልፏል፡፡

በዚህም መሠረት አስተባባሪ ኮሚቴው የዝግጅት ሥራውን በማጠናቀቅ ጥር 15 ቀን 2014 ዓ.ም የፌዴራልና የክልል ፍትህ አካላት ከፍተኛ አመራሮች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በሚገኙበት ኢንተር ሌግዠሪ ሆቴል ከጥዋቱ 5 ሰዓት ጀምሮ የጠበቆች ጠቅላላ ጉባኤን የሚያካሂድ መሆኑን ነው መግለጫው ያስታወቀው።

በዕለቱም የማህበሩ ሥራ አስፋፃሚዎችና ፕሬዚዳንት ምርጫ እንደሚካሄድ ገልጾ፥ አስተባባሪ ኮሚቴው በትናንተናው ዕለት ባከሄደው ስብሰባ የጉባኤ እና ምርጫ ማስፈጸሚያ መመሪያ አፅድቋል ብሏል፡፡

ከፍትሕ ሚኒስቴር የተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦

የኢትዮጵያ ፌዴራል ጠበቆች ጠቅላላ ጉባኤን አስመልክቶ ከኢፌዴሪ የፍትሕ ሚኒስቴር የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ሐምሌ 29 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን የፌዴራል ጥብቅና አገልግሎት ፈቃድ አሰጣጥና አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1249/2013 ማፅደቁ ይታወቃል፡፡

በዚህ አዋጅ አንቀጽ 57 ንዑስ አንቀጽ 1 መሠረት ፈቃድ የተሰጣቸዉ ሁሉንም የፌዴራል ጠበቆች እና የጥብቅና ድርጅቶች በአባልነት ያቀፈ የኢትዮጵያ ፌዴራል ጠበቆች ማህበር በሕግ የተቋቋመ ሲሆን በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 57 ንዑስ አንቀጽ 4 መሰረት ደግሞ ማንኛዉም ፈቃድ የወሰደ ጠበቃና የጥብቅና ድርጅት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የማህበሩ አባል እንደሚሆን ሕጉ በአስገዳጅ ሁኔታ አስቀምጧል፡፡

ፍትሕ ሚኒስቴር አዋጁ ከፀናበት ጊዜ ጀምሮ በሚቆጠር 6 ወር ጊዜ ዉስጥ የመጀመሪያዉን የማህበሩን ጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ የመጥራት እና ሥራ ለማስጀመር የሚያስችሉ የተለያዩ አደረጃጀቶችና ኮሚቴዎችን አቋቁሞ የሽግግር ሥራዉን የማሳለጥ ኃላፊነት ተሰጦታል፡፡

ሚኒስቴር መ/ቤቱ በሕግ የተጣለበትን ይህን ኃላፊነት ለመወጣት በሽግግር ወቅት ያለዉን የአዲሱን አዋጅ አፈጻጸም የሚከታተል እና ጠቅላላ ጉባኤ የሚያመቻች ኮሚቴ ከጠበቆችና ፍትሕ ሚኒስቴር አመራሮችና ባለሙዎችን ያካተተ አስተባባሪ ኮሚቴ ጥቅምት 19 ቀን 2014 ዓ.ም በፍትሕ ሚኒስትሩ ክቡር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ተሰይሞ ሥራዉን ሲያከናዉን ቆይቷል፡፡

በዚህም መሠረት አስተባበሪ ኮሚቴዉ የዝግጅት ሥራዉን በማጠናቀቅ ጥር 15 ቀን 2014 ዓ.ም የፌዴራልና የክልል ፍትህ አካላት ከፍተኛ አመራሮች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸዉ እንግዶች በሚገኙበት በአዲስ አበባ ካሳንችስ አካባቢ በሚገኘዉ ኢንተር ሌግዠሪ (የቀድሞዉ ኢንተር ኮንትኔንታል) ሆቴል ከጥዋቱ 5፡00 ሰዓት ጀምሮ የጠበቆች ጠቅላላ ጉባኤን የሚያካሂድ እና በዕለቱም የማህበሩ ሥራ አስፋፃሚዎችና ፕሬዘዳንት ምርጫ የሚካሄድ ሲሆን አስተባባሪ ኮሚቴዉ በትናንተናዉ ዕለት ማለትም ጥር 13 ቀን 2014 ዓ.ም ባከሄደዉ ስብሰባ የጉባኤ እና ምርጫ ማስፈጸሚያ መመሪያ አፅድቋል፡፡

በፍትሕ ሚኒስቴር የመንግስት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ድኤታ እና የአስተባባሪ ኮሚቴዉ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ዓለምአንተ አግደዉ እንደገለጹት የኢትዮጵያ ፌዴራል ጠበቆች ጠቅለላ ጉባኤ ሲካሄድ በአገራችን ታሪክ የመጀመሪ መሆኑን ጠቅሰዉ ለአገራችን የፍትህ ስርዓትና ለሙያዉ ዕድገት ብሎም ለሕረተሰቡ የተሻለ የፍትሕ አገልግሎት ለመስጠት ወሳኝ ሚና ያለዉ መሆኑን ከግምት በማስገባት ሁሉም የፌዴራል ጠበቆች በነቂስ ወጥተዉ በጠቅለላ ጉባኤዉ ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.