Fana: At a Speed of Life!

አሸባሪው የህወሓት ቡድን ከፍተኛ ሰብዓዊና ምጣኔ ሐብታዊ ውድመት ማድረሱን ጥናት አረጋገጠ

አዲስ አበባ፣ ጥር 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው የህወሓት ቡድን በፈፀመው ወረራ በሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ሰብዓዊና ምጣኔ ሀብታዊ ውድመት መድረሱን በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የተሰራ ጥናት አረጋገጠ።

ዩኒቨርሲቲው አሸባሪ ቡድኑ በሰሜን ሸዋ ዞን ያደረሰውን ሁሉን አቀፍ ማኅበራዊ ቀውስ በስድስት የጥናትና አራት የመልሶ ማቋቋም ቡድኖች ተመልክቷል፤ በጥልቀትም አጥንቷል ነው የተባለው፡፡

የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ በጉዳዩ ላይ እያካሄዳቸው ያሉትን የተለያዩ የምርምርና መልሶ የማቋቋም ፕሮጀክቶችም የማስተዋወቅ ሥራ እየሰራ ይገኛል፡፡

የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ንጉስ ታደሰ ÷ ዩኒቨርሲቲው ታሪክን በአግባቡ ከመሰነድ በተጨማሪ፥ በመረጃ ላይ የተመሰረተ የመልሶ ማቋቋም ሥራ ለመስራት እንዲቻል የጥናት ቡድኖችን በቦታው በማሰማራት ጥናት ማካሄዱን እና መረጃዎችን የመሰነድ ስራ ማከናወኑን ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው በጥናትና ምርምሩ ብቻ ሳይሆን በመልሶ ማቋቋምና ግንባታ ሥራውም ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ እንደሚያደርግ ነው ፕሬዚዳንቱ የተናገሩት።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለም ÷ በርካታ የጥናትና ምርምር እንዲሁም የማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ሥራዎችን ያበረከተው የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በህልውና ዘመቻው ወቅት ለነበረው ተሳትፎ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ዩኒቨርሲቲው በሰላሙ ወቅት ትውልድ ሲያንጽ በህልውና ዘመቻ ወቅት ደግሞ ሀገርን ለማዳን ሲተጋ ነበር ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ÷ በግምት ሲገለጽ የነበረው አሸባሪው የህወሃት ቡድን የፈጸመው ጉዳት ተጠንቶና ተተንትኖ እንዲቀርብ በክልሉ ያሉ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች እየሠሩ መሆናቸውንም አሳውቀዋል።

አጠቃላይ የተጋድሎና የውድመት ግኝቱ በመጽሐፍ መልክ ታትሞ ትውልድ እንዲማርበት እየተሰራ ነውም ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ ዶክተር ይልቃል ከፋለ።

በሳምራዊት የስጋት

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.