Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል በ6 ወራት ውስጥ ከ193 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በመስኖ ማልማት መቻሉን ቢሮው ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥር 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በ6 ወራት ውስጥ 193 ሺህ 634 ሄከታር መሬት በመስኖ ልማት መሸፈን መቻሉን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ።

በመስኖ ልማት ከተያዘው ዕቅድ 82 ከመቶ ተፈፅሟል ተብሏል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የ2014 ዓ.ም የግብርና ልማት ዘርፍ እና ተጠሪ ተቋማት የ6 ወር እቅድ ክንውን ግምገማ በደሴ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

ከዚህ ውስጥ 80ሺህ ሄክታር መሬት የመስኖ ስንዴ በማልማት፥ 3 ሚሊየን 600 ሺህ ኩንታል ምርት ለማምረት የታቀደ ሲሆን፥ 54 ሺህ 709 ሄክታር በመለየት እና 38 ሺህ 838 ሄክታር በማረስ ከ34 ሺህ ሄክታር በላይ በዘር መሸፈን ችለናል ሲሉ የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ቃልኪዳን ሽፈራው አብራርተዋል።

በውይይቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ፥ ባለፉት 6 ወራት ኢኮኖሚያችን በጦርነትና በተለያዩ ምክንያቶች ተጎድቶ በመቆየቱ የእቅድ ግምገማው በቀጣይ ለሚኖረን ስምሪት መሠረት የሚጥል ነው ብለዋል።

ለ2 ቀናት በሚቆየው የዕቅድ ግምገማ የዘርፉ የ6 ወራት አፈፃፀም ላይ ውይይት የሚካሄድ ይሆናል።

በክልሉ በ2013/14 የምርት ዘመን በአጠቃላይ 4 ሚሊየን 594 ሺህ 210 ሄክታር መሬት በማልማት፤ 131 ሚሊየን 885 ሺህ 998 ኩንታል ምርት ለማምረት፣ 1 ሚሊየን 513 ሺህ 381 ሄክታር በገቢ ማስገኛ ሰብሎች ለመሸፈን ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.