Fana: At a Speed of Life!

35ኛው የህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ  በሰላም እንዲጠናቀቅ የጋራ ግብረ ኃይሉ በቂ ዝግጅት ማድረጉን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ጥር 19፣2014(ኤፍ ቢሲ) 35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤና 40ኛው የህብረቱ ስራ አስፈፃሚ ስብሰባ በሰላም_እንዲጠናቀቅ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ዝግጅቱን አጠናቆ ወደ ስምሪት መግባቱን ገልጿል።

በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አስተባባሪነት የሚመራው የሪፐብሊካን ጋርድ፣ የብሄራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት፣ የአዲስ አበባ ፖሊስና የኦሮሚያ ፖሊስን ያካተተው የፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ በሰላም እንዲጠናቀቅ የሚያስችሉ ተግባሮች ያሉበትን ደረጃ ገምግሟል።

በፀረ- ሰላም ኃይሎች እንቅስቃሴ ላይ የሚደረግ የክትትል ደረጃ፣ አመራርና አባሉ በእቅድ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ ማግኘቱን፣ በሰው ኃይልና በሎጂስቲክ ያለውን ዝግጅት እንዲሁም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ያለውን ቅንጅትም ቃኝቷል፡፡

ግብረ ኃይሉ ባደረገው ግምገማ በቅድመ ዝግጅት ስራ፣ በመረጃ ልውውጥ፣ የፀጥታ ኃይሉ በጋራም ሆነ በተናጠል መስራት የሚገባው ኃላፊነቶች እንዴት እንደተከናወኑ፣ የሽብር ተግባሮችን አስቀድሞ ማክሸፍ የሚያስችሉ ልምምዶች፣ ህግ አስከባሪዎች ህግን ለማስከበር ያላቸው ቁመና ላይ ተወያይቶ የተገለፁት ጉዳዮች በላቀ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ አስቀምጧል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ  ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ግምገማውን በመሩበት ወቅት እንግዶቹ በሚንቀሳቀሱባቸው ቦታዎች ሁሉ ለየት ያለ ትኩረት በመስጠት አካባቢዎችን ፈትሸው ከማንኛውም የፀጥታ ችግር የፀዱ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ካሉ በኋላ፥ በአፍሪካ ህብረት አካባቢ፣ እንግዶች በሚያርፉባቸው ስፍራዎች ሞተረኛና እግረኛ ትራፊክ ፖሊስ እና የወንጀል መከላከል አባላት ተገቢውን ቦታ በመያዝ የተግባር ልምምድ እንደሚያደርጉም ገልፀዋል፡፡

ኮሚሽነር ጀነራሉ በሽብር ዙሪያ በተካሄዱ ጥናቶች መሰረት አስቀድመን ኦፕሬሽን በማካሄድ አካባቢዎችን ማፅዳት ይገባናል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽነር ጀነራሉ አያይዘውም ክንውኑ ዘረፋዎችን ጨምሮ ሌሎች  የተደራጁ የወንጀል ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረጉ ዘመቻዎችን ማካሄድ፣ የፀጥታ ችግሮችን አስቀድሞ መከላከል የሚችል ትጥቅና ሌሎች የሎጀስቲክ ግብዓቶች የተሟሉለት ኃይል ማዘጋጀት ይጠይቃል ካሉ በኋላ መሪዎቹ ወደ አዲስ አበባ ሲገቡና ጉባኤው በሚጀመርበት ወቅትም የተጠናከረ ጥበቃና እጀባ ማካሄድ፣ የትራፊክ ፍሰቱን ማሳለጥ፣ የተቀናጀ አመራርና የመረጃ ፍሰት እንዲኖር ማድረግ ይገባል፤ ፍፁም ጨዋነት የተላበሰ አገልግሎት መስጠትም ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በስብሰባው ላይ የሚሳተፉ መሪዎችን ከማንኛውም የወንጀል ስጋትና አደጋ በመከላከል ስብሰባው ያለ ምንም የፀጥታ ችግር በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ከወትሮው በተለየ መልኩ በቂ ዝግጅት በማድረግ ስምሪት ወስዶ ወደ ተግባር መግባቱ ተገልጿል፡፡

የጋራ ግብረ ኃይሉ የአውሮፕላን ማረፊያ፣ የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣ የመዝናኛ ቦታዎች፣ እንዲሁም እንግዶች በሚንቀሳቀሱባቸው የገበያ ማዕከላት፣ የሚዘዋወሩባቸውን አካባቢዎችና የሚጎበኟቸውን ቦታዎች ሁሉ ደህንነታቸው የተረጋገጠ ለማድረግና ስብሰባው ፍፁም ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሙሉ ዝግጅት ማድረጉም ተጠቁሟል፡፡

በሁሉም አካባቢዎች በርካታ የፀጥታ አካላት ማሰማራቱንና መሪዎች በሚሰበሰቡበት አካባቢ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያደርግም የጋራ ግብረ-ኃይሉ አስታውቋል፡፡

የህወሃት ጁንታ ቡድንና ርዝራዦቹ  እንዲሁም ሰላማችንን ለማወክ ሌት ተቀን የሚሰሩ ሌሎች አሸባሪ ቡድኖች ይህንን ስብሰባ ለእኩይ ተግባራቸው እንደ መልካም አጋጣሚ ሊጠቀሙበት ስለሚችሉ የጋራ ግብረ-ኃይሉ ህጋዊ እርምጃ በአሸባሪዎች ላይ ለመውሰድ በተጠንቀቅ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።

ስለሆነም የሰላሙ ባለቤት የሆነው መላው ህዝብ ይህንን ተገንዝቦ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባና አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙት በፍጥነት ለጋራ ግብረ-ኃይሉ በስልክ ቁጥሮች +251115-52-63-03፣ +251115-52-40-77፣ +251115-54-36-78 እና +251115-54-36-81 እንዲሁም በ987፣ 991 እና 816 ነፃ የስልክ መስመሮች ጥቆማ በመስጠት ወይም በአካባቢው ለሚገኝ የፀጥታ ኃይል መረጃውን በአካል በማድረስ የተለመደ ድጋፍና ትብብሩን እንዲያደርግ ጥሪ ማስተላለፉን ከፌዴራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

 

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.