Fana: At a Speed of Life!

ሦስት የአንድ ቤተሰብ አባላትን በቦምብ የገደሉት አባትና ልጆች በእድሜ ልክ እና በ25 ዓመት ፅኑ እሥራት ተቀጡ

አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰሜን ሸዋ ዞን መንዝ ላሎ ምድር ወረዳ ሦስት የአንድ ቤተሰብ አባላትን በቦምብ የገደሉት አባትና ልጆች በእድሜ ልክ እና በ25 ዓመት ፅኑ እሥራት ተቀጡ።

1ኛ ተከሳሽ ዓለምነው ቀማው ወልደፃዲቅ እና 3ኛ ተከሳሽ አብርሃም ቀማው ወልደፃዲቅ በእድሜ ልክ እንዲሁም 2ኛ ተከሳሽ ወልደፃዲቅ ገብረማሪያም በ25 ዓመት ጽኑ እሥራት እንዲቀጡ ነው የተፈረደባቸው።

በወረዳው የ07 ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ተከሳሾቹ አስቀድመው ሰውን ለመግደል በማሰብ ጥር 17 ቀን 2012 በግምት ከምሽቱ 1 ሰዓት በሚሆንበት ጊዜ በቀበሌው ጦል ጎጥ ልዩ ስሙ ሾላ ተብሎ ከሚጠራው ስፍራ 1ኛ ተከሳሽ ዓለምነው ቀማው ወልደፃዲቅ ከሟች ወንድወሰን ወልደፃዲቅ የሳር መኖሪያ ቤት ላይ በመስኮት ቦምብ ወርውሮ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ሟችን በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሏል ይላል የአቃቤ ህግ የክስ መዝገብ።

ተከሳሾቹ በሟች ወንድወሰን ወልደፃዲቅ መኖሪያ ቤት የነበሩትን የዘጠኝ ወር ነፍሰጡሯን ሟች ቡጥቃ ወንድወሰንን እና ሟች ማሚቱ ተክለሀይማኖትን በ1ኛ ክስ ላይ በተጠቀሰው ጊዜና ቦታ በተመሳሳይ ጨካኝነትና ነውረኝነት በተሞላበት ሁኔታ 1ኛ ተከሳሽ አለምነው ቀማው ወልደፃዲቅ በሟች ወንድወሰን ወልደፃዲቅ መኖሪያ ቤት ላይ በመስኮት ቦምብ ወርውሮ ሟቾቹን በአሰቃቂ ሁኔታ የገደላቸው መሆኑን መዝገቡ ያስረዳል።

2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች ደግሞ የአንደኛ ተከሳሽን ሃሳብና አድራጎት በሙሉ ሃሳባቸው ተቀብለው የግል ተበዳይን ቤት በመቆለፍ ሟችን በአሰቃቂ ሁኔታ ሕይወቱ እንዲያልፍ በማድረጋቸው በከባድ የሰው መግደል ወንጀል የዞኑ አቃቤ ህግ ክስ መስርቷል፡፡

አቃቤ ህግ በመሰረተው 4ኛ ክስ ደግሞ ተከሳሾቹ በ1ኛ ክስ ላይ በተጠቀሰው ጊዜና ቦታ 1ኛ ተከሳሽ ዓለምነው ቀማው ወልደፃዲቅ ከሟች ቤት የነበረችውን የግል ተበዳይ በለጥ ወንደሰንን ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በፈነዳው ቦምብ ፍንጣሪ የተለያዩ የሰውነት ክፍሏ ላይ ከባድ የአካል ጉዳት ማድረስ ክስ ቀርቧል፡፡

2ኛ እና 3ኛ ተከሳሶች የግል ተበዳይን ቤት በመቆለፍና በመያዝ የግል ተበዳይዋ ከባድ የአካል ጉዳት እንዲደርስባት በማድረጋቸው ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡

ከ2ኛ ተከሳሽ ውጪ ያሉት ተከሳሾች ያልተያዙ በመሆኑ እንዲሁም ፍርድ ቤቱ ተደጋጋሚ ጥሪ ቢያደርግም ሊቀርቡ ባለመቻላቸው ጉዳያቸው በሌሉበት እንዲታይ የተወሰነ ሲሆን ፥ 2ኛ ተከሳሽ ግን ከመንግስት በተመደበለት ጠበቃ እየታገዘ የዕምነት ክህደት ቃሉን ሲጠየቅ ወንጀሉን አልፈጸምኩም ሲል ክዶ ተከራክሯል፡፡

ዐቃቤ ህግም ክሱን ያስረዱልኛል ያላቸውን የሰውና የሰነድ ማስረጃ በማቅረብ ለፍርድ ቤቱ አሰምቷል፡፡

ግራ ቀኙን የተመለከተው ፍርድ ቤቱ ተከሳሾችን ጥፋተኛ በማለት እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል፡፡

ተከሳሾች ሊከላከሉ ባለመቻላቸው ጥፋተኛ ናችሁ በማለትም ወስኗል፡፡

የግራ ቀኙን የቅጣት ማቅለያና ማክበጃ ሃሳብ የተቀበለው የሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጥር 16 ቀን 2014 በዋለው ችሎት ተከሳሾችን ያርማል ሌሎችን ያስተምራል በሚል ፥ 1ኛ እና 3ኛ ተከሳሽን በዕድሜ ልክ ጽኑ አሥራት፣ 2ኛ ተከሳሽን ደግሞ በ25 ዓመት ጽኑ እሥራት እንዲቀጡ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

እንዲሁም ተከሳሾቹ ለ3 ዓመት ከህዝባዊ መብታቸው እንዲታገዱ ውሳኔ የሰጠ ሲሆን፥ ፖሊስም ያልተያዙ ተከሳሾችን አፈላልጎ ለደብረ ብርሃን ማረሚያ ቤት እንዲያስረክብ ማዘዙን ከዞኑ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በአበበ የሸዋልዑል

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.