Fana: At a Speed of Life!

በግማሽ ዓመቱ 11 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2014 (ኤፍ ቢሲ) በግማሽ ዓመቱ የፀጥታ ችግር ያለባቸው አካባቢዎችን ሳይጨምር 11 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከፍተኛ ሥራ አመራሩ ለሶስት ቀናት በጎንደር ከተማ ባካሄደው የ2014 በጀት ዓመት የመጀመሪያ መንፈቅ ዓመት የሥራ አፈፃፀም ግምገማ ላይ 176 ሺህ 97 አዳዲስ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ ተገልጿል፡፡
ከአዳዲስ ደንበኞቹ መካከል 91 ከመቶ የሚሆኑት የድህረ-ክፍያ ቆጣሪ ያገኙ ሲሆን፥ 9 ከመቶው የሚሆኑት ደግሞ የቅድመ-ክፍያ ተጠቃሚ መሆናቸውን በቀረበው ሪፖርት ተመላክቷል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ተቋሙ በግማሽ ዓመቱ የፀጥታ ችግር ያለባቸው አካባቢዎችን ሳይጨምር ከሀይል ሽያጭ 8 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር፣ ከአዲስ ደንበኞች የኤሌክትሪክ መስመር ማስቀጠያ መዋጮ 2 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር፣ ከንብረት ማስወገድና ከልዩ ልዩ 32 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር በድምሩ ከ 11 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ እንደተሰበሰበ ተገልጿል፡፡
ተቋሙ በዘረጋቸው ዘመናዊ የክፍያ አማራጮች አማካኝነት 363 ሺህ 675 ደንበኞች ወርሃዊ የፍጆታ ሂሳባቸውን የተመቻቹ የክፍያ አማራጮችን በመጠቀም መክፈላቸውም ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡
ሆኖም አሁንም ብዙ የድህረ-ክፍያ ተጠቃሚ ደንበኞች ወርሃዊ የፍጆታ ክፍያቸውን በጥሬ ገንዘብ እየከፈሉ ስለሆነ፤ ተቋሙ በዘረጋቸው ዘመናዊ የክፍያ አማራጮች አማካኝነት ተጠቅሞ በመክፈል ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን እንዳያባክኑ በግምገማው ወቅት ተነስቷል፡፡
የውጭ ምንዛሪ ችግር፣ በአንዳንድ ክልሎች የሚስተዋለው የጸጥታ ችግር ምክንያት በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ የሚደርሰው ውድመት፣ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ከውጭ የሚገቡ አቅርቦት መዘግየት በግማሽ ዓመቱ ለሥራ አፈፃፀሙ ማነቆዎች እንደነበሩ መመላከቱን ከአገልግሎቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.