Fana: At a Speed of Life!

ጤና ሚኒስቴር ከአጋር አካላትያሰባሰበውን ከ21 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ አስረከበ

አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጤና ሚኒስቴር ከአጋር አካላት ያሰባሰበውን ከ21 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ አስረከበ፡፡
 
የጤና ሚኒስቴር በአማራና አፋር ክልሎች በአሸባሪው ህወሓት ወረራ የወደሙ ተቋማትን የጉዳት ደረጃ በማጥናትና ድጋፍ ሰጪ አጋር አካላትን በማማከር የመልሶ ማቋቋም ስራ እየሰራ መሆኑ ይታወቃል፡፡
 
በዚህም ከአጋር አካላት ጋር በአማራ ክልል የሚገኙ አምስት ጤና ጣቢያዎች እና ሦስት የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎችን ከቀዶ ጥገና ጠረጴዛ እና ማደንዘዣያ ማሽን በቀር ሙሉ በሙሉ አስፈላጊው ቁሳቁስ እንዲሟላላቸው ማድረጉ ተገልጿል፡፡
 
በጤና ሚኒስቴር በእናቶችና ህጻናት ዳሬክቶሬት የእናቶች ጤና ቡድን አስተባባሪ ሲስተር ዘምዘም ሙሃመድ÷ለስምንቱ ተቋማት የጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ማህጸንና ጽንስ ሀኪሞች ማህበር በጋራ ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል፡፡
 
የጤና ተቋማቱን መልሶ ለማቋቋምም ከ2 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ነው አስተባባሪዋ የገለጹት፡፡
 
ከዚህም ባለፈም ሚኒስቴሩ ሌሎች አጋሮችን በማስተባበር በአይነትና በጥሬ ገንዘብ ከ21 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ አሳባስቦ ለአማራ ክልል ጤና ቢሮ ማስረከቡን በጤና ሚኒስቴር የህፃናትና የእናቶች ጤና ዳይሬክተ ዶ/ር መሠረት ዘላለም ተናግረዋል፡፡
 
ድጋፉን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ አብዱከሪም መንግስቱ የተረከቡ ሲሆን÷ ለተደረገው ድጋፍ አጋር አካላትንና የጤና ሚኒስቴርን አመስግነዋል፡፡
 
በአለባቸው አባተ
 
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.