Fana: At a Speed of Life!

ከተማ አስተዳደሩ የ6 ወር የስራ አፈፃፀሙን ገመገመ

አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፉት 6 ወራት የተከናወኑ የማዕከል የአስፈፃሚ አካላት የእቅድ አፈፃፀም ያለበትን ደረጃ በዛሬው እለት በዝርዝር ገምግሟል፡፡

የከተማዋ ፕላን ኮሚሽን ባቀረበው ሪፖርት አፈፃፀም ላይ ተመስርቶ የተወያየው ከተማ አስተዳደሩ በዋነኝነት አጠቃላይ የእቅዱ ስኬት መለኪያ ከተማዋ ትደርስበታለች ተብሎ ከተቀመጠው የ10 እና የ5 ዓመት ትልምና ከዚያ ተወስዶ በተዘጋጀው የአመት እቅድ መነሻ ላይ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በግምገማው ማጠቃለያ የስራ አቅጣጫዎችን ያስቀመጡት የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ÷ ከተማው ባለፉት ወራት አንድም ጦርነቱን በተጋፈጠችበት ሁኔታ የሰላምና የፀጥታ ስራዎችን የሚያስተባብር ሃይል እንዳለ ሁሉ የመንግስት ስራዎችን ልክ እንደ ጦርነት ግንባር በልዩ ትኩረትና ክትትል እንዲመራ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡

በዚህም የተሻለ አፈፃፀም ያላቸውና በህዝብም ጭምር የተመሰከረላቸው እንደ ምገባ ስራ፣ የህብረተሰብ ተሳትፎ ስራዎች፣ ፅዳትና ውበት፣ ሰላምና ፀጥታ፣ ትምህርት፣ ጤና እና የገቢ ዘርፎች ተጠቃሽ ተቋማት መኖራቸውን ከንቲባዋ ተናግረዋል።

የበጎ ፍቃድ ስራዎች በአጠቃላይ ህብረተሰቡን በማንቀሳቀስ በአካበቢ ሰላም ማስከበር ላይ ፥ ከ18 ሺህ በላይ አደረጃጀቶች ተፈጥረው በሶስት ፈረቃ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ጭምር ተጋፍጠው ከተማዋን ሲጠብቁ የነበረበትን የተቀናጀበትና የተመራበት አግባብ አበረታች እንደነበር ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም ዝቅተኛ አፈፃፀም ያላቸው ተቋማትም ጉድለታቸውን አርመው በቀጣይ ህዝቡን ጥያቄዎች በላቀ ደረጃ ለመፈፀም መዘጋጀት እንዳባቸውም አሳስበዋል፡፡

በአጠቃላይ ከተማ መሰረታዊ ግብ ተብሎ የተቀመጠው ተቋማዊ ስርዓት መፍጠር በሰዎች ጥንካሬና ድክመት ላይ ያልተመሰረቱ ስርዓታዊ የሆነ ጠንካራ ተቋማትን መፍጠር ነው ብለዋል፡፡

ይህም በሁሉም ተቋማት መሰረታዊ ተልእኮ መሆኑንም አስምረውበታል።

የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው፥ በከተማዋ ተቋማት ላይ የተጀመሩት የተቋማዊ ለውጥ ስራዎች ከፍተኛ ክትትል ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

በጥቅሉ ከነበረው አስቸጋሪ ሃገራዊ ሁኔታ አንፃር አበረታች አፈፃፀሞች መኖራቸው የተገለፀ ሲሆን፥ ሆኖም ግን የህዝቡን ጥያቄዎች በብቃት ለመመለስ በቀጣይ የክፍለ ከተሞችና ልማት ድርጅቶችንም አካቶ በዝርዝር ተገምግሞ ለቀጣይ አፈፃፀም ጠንካራ ርብርብ እንደሚደረግም መገለጹን ከከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.