Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ የጀግንነት ምንጭ ለሆኑ የሠራዊት አባላት እውቅና መስጠት የሀገር ኩራት ነው -ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) “አሸባሪው የህውሃት ቡድንን በመደመሰስ ጀብዱ የፈጸሙ የኢትዮጵያ የጀግንነት ምንጭ ለሆኑ የሠራዊት አባላት የሜዳልያ ሽልማት መስጠት የሀገር ኩራት ነው” ሲሉ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።
የማዕከላዊ ዕዝ በተሰለፈባቸው አውደ ውጊያዎች የላቀ ድል ላስመዘገቡና ጀብዱ ለፈጸሙ የሠራዊት አባላትና አመራሮች ዛሬ የማዕረግ ዕድገት፣ ሽልማትና ዕውቅ ተሰጥቷል።
የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በሥነስርዓቱ ላይ እንዳሉት፥ የሀገር መከላከያ ሠራዊት በህግ ማስከበርና በህብረ ብሄራዊ ዘመቻዎች የተሰጠውን ተልዕኮ በድል ተወጥቷል።
የአሸባሪው ህወሓት ሀገር የማፍረስ ሴራ ለማክሸፍ የመከላከያ ሠራዊት አስቸጋሪ መልክዓ ምድርና የአየር ፀባይ ሳይበግረው ትልቅ ተጋድሎ መፈፀሙን ገልፀዋል።
ከሰሜን ሸዋ ዞን ጀምሮ በተካሄዱ ተከታታይ ውጊያዎች የአሸባሪ ቡድኑን ሽንፈት ያከናነቡና ጀብድ የፈፀሙ የሠራዊት አባላትን ሜዳሊያ መሸለም የኢትዮጵያ ኩራት ነው ብለዋል።
ይህም ካለፉት ዘመቻዎች ያገኙትን ልምድ በመጠቀም የአሸባሪ ቡድኑ እስኪደመሰስ ድረስ በሚካሄዱ ውጊያዎች በጠላት ላይ የተለመደውን ድል እንዲያስመዘግቡ መነሳሳት ይፈጥራል ነው ያሉት።
“የዛሬ የሜዳሊያ ተሸላሚ ጓዶች ያገኛችሁትን ሜዳሊያ የቤተሰብ፣ የጎረቤትና የሀገር ክብር በመሆኑ ወደ ቤተሰቦቻችሁ ላኩትና በክብር ያስቀምጡላችሁ” ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ይህ የሽልማት ሥነስርዓት ከሠራዊት ግንባታ ሂደት ጋር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አረጋግጠዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይም በአውደ ውጊያ ጀብድ የፈፀሙ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃ የሜዳሊያ ሽልማትና የማዕረግ ዕድገት ማልበስ ሥነስርዓት መካሄዱን ኢዜአ ዘግቧል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.