Fana: At a Speed of Life!

በሳዑዲ እስር ቤቶች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አያያዝ ስለሚሻሻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ተደረገ

አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ የተመራ እና ከመንግስት የስራ ሃላፊዎችና ከሃይማኖት ተቋማት መሪዎች የተውጣጣ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ልዑካን ቡድን በሳዑዲ አረቢያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት አድርጓል።

የልዑካን ቡድኑ የጉዞ ዓላማ የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት የበለጠ ስለሚጠናከርበት እንዲሁም በሳዑዲ ዓረቢያ የሚገኙ ዜጎችን የአጭር ጊዜና ዘላቂ መፍትሄዎች ስለሚያገኙበት ሁኔታ ከከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ለመምከር መሆኑ ተገልጿል፡፡

ቡድኑ ባለፉት አራት ቀናት በነበረው ቆይታ በሪያድ ከኢትዮጵያ ኮሙዩኒቲ አመራሮች እና አባላት፣ ከሀይማኖት መሪዎች እንዲሁም ከንግዱ ማህበረሰብ አባላት ጋር ተወያይቷልም ነው የተባለው፡፡

በውይይቱ ወቅትም እስር ቤት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አያያዝ ስለሚሻሻልባቸው ጉዳዮች፣ የመኖሪያ ፈቃዳቸው የተቃጠለና የተለያዩ ቅጣቶች የሚጠብቋቸው ነገር ግን በራሳቸው ገንዘብ ተሳፍረው አገራቸው መግባት ለሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ቅጣት ተነስቶላቸውና ምህረት ተደርጎላቸው ወደ ሀገራቸው መመለስ በሚችሉባቸው አግባቦች ዙሪያም ውይይት መደረጉ ተገልጿል፡፡

እስር ቤት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በተቻለ ፍጥነት ዝግጅት ተደርጎ ወደ ሀገራቸው በሚመለሱበት እና ይህንን ችግር በመፍታት የሁለቱን ሀገሮች ስትራቴጂካዊ ትብብርና ግንኙነት ወደላቀ አጋርነት ማሸጋገር በሚቻልባቸው አግባቦች ዙሪያ ጠቃሚ እንዲሁም ለቀጣይ መተማመንና ትብብር አዲስ ምዕራፍ ለመክፈት ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ተገኝቷልም ነው የተባለው።

በዚህም መሰረት ለቅድመ ዝግጅት እንዲያግዝ በኢትዮጵያ በኩል ቅድሚያ የሚሰጣቸዉን ተግባራት የመለየት ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ መባሉን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

 

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.