Fana: At a Speed of Life!

ማዕከሉ አገራዊ የምክክር መድረኩ ተልዕኮ እንዲሳካ መገናኛ ብዙሃን ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል አለ

አዲስ አበባ፣ ጥር 23 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ስለ አገራዊ የምክክር መድረኩ ኅብረተሰቡ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖረውና ተልዕኮው እንዲሳካ መገናኛ ብዙሃን የተዛቡ አመለካከቶችን የሚያጠሩ ስራዎችን ተደራሽ በማድረግ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የሕገ መንግስትና ፌዴራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል አስታወቀ።

ማዕከሉ ውይይት በሚሹ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ኅብረተሰቡ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

በፌዴራሊዝም፣ ሕገ መንግስት፣ ሕገ መንግስታዊነትና የመገናኛ ብዙሃን ሚና ዙሪያ ማዕከሉ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የመጀመሪያ ዙር የአሰልጣኞች ስልጠና መስጠት ጀምሯልም ነው የተባለው።

ማዕከሉ በአገር ውስጥ ተመዝግበው ከሚንቀሳቀሱ ከ200 በላይ መገናኛ ብዙሃን 50 ዎቹን በመምረጥ ባደረገው የፍላጎት ዳሰሳ ጥናት መሰረት ነው ስልጠናውን መስጠት የጀመረው ሲሉ የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኃይለኢየሱስ ታዬ ተናግረዋል፡፡

ስልጠናው በቀጣይም በትምህርት ቤቶች፣ በሲቪክ ማኅበራትና በሌሎች ተቋማት ለሚሰሩ ባለሙያዎች እንደሚሰጥ ነው የተገለጸው።

የማዕከሉ አሰልጣኝ አቶ ኖህ ያደሳ፥ ኅብረተሰቡ ወደ አገራዊ ምክክር ከመግባቱ አስቀድሞ በውይይቱ ሊነሱ በሚችሉ ርዕሰ ጎዳዮች ላይ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግም ያስፈልጋል ብለዋል።

በሕገ መንግስት፣ በፌዴራሊዝምና በሕገ መንግስታዊነት ላይ ኅብረተሰቡ ትክክለኛ መረጃ ይዞ ወደ አገራዊ ምክክር እንዲገባ ማድረግ ደግሞ የማዕከሉ ኃላፊነት መሆኑንም ኢዜአ ዘግቧል።

ማዕከሉ በሕገ መንግስትና ፌዴራሊዝም ዙሪያ አስተምህሮ በመስጠት ንቃተ ሕገ መንግስቱ ያደገና የፌዴራሊዝም አስተሳሰቡ የዳበረ ኅብረተሰብ የመፍጠር ተልዕኮ ኖሮት በአዋጅ 1123/2011 የተቋቋመ መሆኑ ይታወሳል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.