Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል ከ37 ሺህ በላይ ተማሪዎች ከነገ ጀምሮ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ይወስዳሉ

አዲስ አበባ፣ ጥር 23 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል አሸባሪው ህወሓት በፈፀመው ወረራ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ሳይወስዱ ለቆዩ 37 ሺህ 55 ተማሪዎች ከነገ ጀምሮ ፈተናው እንደሚሰጥ የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው የፈተና ዝግጅትና አስተዳደር ተወካይ ቡድን መሪ አቶ ኃይሉ ታምር እንደገለጹት÷ ፈተናው የሚሰጠው ከነገ ጀምሮ ለአራት ተከታታይ ቀናት ነው።

ፈተናው በሰሜንና ደቡብ ወሎ ዞኖች፣ በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን አስተዳደርና በደሴ ከተማ አስተዳደር ሙሉ በሙሉ እንደሚሰጥ አሳውቀዋል፡፡

ፈተናው በዋግ ኽምራ ዞን ከአበርገሌ ወረዳ በስተቀር በሁሉም ወረዳዎች፣ በሰሜን ሸዋ ዞን ሶስት ወረዳዎች እና በሰሜን ጎንደር ዞን በአንድ ጣቢያ ፈተናው እንደሚሰጥ አስረድዋል።

በኦሮሚያ ክልል ከምስራቅ እና ምዕራብ ወለጋ ዞኖች ተፈናቅለው ለመጡ 220 የክልሉ ተወላጅ ተማሪዎችም በቡሬ ከተማ በተዘጋጀ የፈተና ጣቢያ ፈተናው እንደሚሰጥ አቶ ኃይሉ ተናግረዋል።

ለብሔራዊ ፈተና ከሚቀመጡት ተማሪዎች መካከል 34 ሺህ 970 የሚሆኑት መደበኛ ተማሪዎች ሲሆኑ÷ ቀሪዎቹ የግል ተፈታኞች ናቸው ተብሏል።

ፈተናው በአጠቃላይ በ129 ጣቢያዎች እንደሚሰጥ ጠቁመው÷ ፈተናውን የሚወስዱ ተማሪዎች ቀደም ሲል በፀጥታ ምክንያት ሳይፈተኑ የቀሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ለፈተናው የሚያስፈልጉ ቁሶችና የመፈተኛ ወረቀቶች ወደተዘጋጁ የመፈተኛ ጣቢያዎች ተጓጉዘው አስፈላጊው ጥበቃ እየተደረገ መሆኑን ያስረዱት ተወካዩ÷ለ ፈተናው ከ1 ሺህ 330 የሚበልጡ ፈታኝ መምህራን፣ ሱፐርቫይዘሮችና ተቆጣጣሪዎች መመደባቸውን መናገራቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመላክታል።

ፈተናው ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲካሄድም በተዘጋጁ የፈተና ጣቢያዎች የፀጥታ አካላት እንዲመደቡ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.