Fana: At a Speed of Life!

የበለጸገች አፍሪካን ለማየት በአህጉሪቷ የሚፈጠሩ ግጭቶችን ማስወገድ እንደሚገባ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ጥር 25፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) የበለጸገች አፍሪካን ለማየት በአህጉሪቷ የሚፈጠሩ ግጭቶችን ማስወገድ ይገባል ሲሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምክትል ዋና ጸሃፊ እና የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ስራ አስፈጻሚ ቬራ ሶንግዌ ተናገሩ፡፡
ስራ አስፈፃሚዋ የአፍሪካ ሕብረት 40ኛው የስራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር ÷በአፍሪካ የሚፈጠሩ የሽብር ተግባራት እና ግጭቶች አሁንም የአህጉሪቷ ስጋት ሆነው መቀጠላቸውን አንስተዋል፡፡
ስለሆነም የበለፀገች አፍሪካን ለማየት የአህጉሪቷ ሙሉ አቅም ግጭትና የሽብር ተግባራትን መከላከል ላይ ሊውል ይገባል ነው ያሉት፡፡
ከግጭት በተጨማሪ የአየር ንብረት ለውጥ ፣ የሳይበር ጥቃት፣ የኮሮና ቫይረስ ወረረሽን፣ የስራ አጥነት ቁጥር መጨመር እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ሌሎች የአህጉሪቷ ስጋቶች መሆናቸውን ስራ አስፈፃሚዋ ተናግረዋል፡፡
በተለይም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በአፍሪካ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ መስተጋብር ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ ማድረሱን ጠቁመዋል፡፡
አፍሪካ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እያገገመች መሆኑን የተናገሩት ስራ አስፈፃሚዋ÷ በወረርሽኙ የተጎዳው የአህጉሪቱ ኢኮኖሚ ግን መልሶ ማገገም አለመቻሉን ነው የገለጹት፡፡
በ2014 በተደረገው የሀገራቱ የነፍስ ወከፍ ገቢ ጥናት መሰረት አራት ሀገራት በከባድ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ የነበሩ ሲሆን÷ አሁን ላይ ግን 17 ሀገራት በከባድ የአኪኖሚ ቀውስ ውስጥ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
አፍሪካውያን መሪዎች የአፍሪካን የኢኮኖሚ ማነቆዎች የሚፈትሹበት ጊዜው አሁን ነው ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በሀገሪቱ የፍጆታ ምርቶች ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱን እና ከአምስት አፍሪካውያን አንዱ በየቀኑ ምግብ አያገኝም ብለዋል ስራ አስፈጻሚዋ፡፡
በዚህም በአህጉሪቱ የሥረዓተ ምግብ እጥረት ሳቢያ በርካታ ህፃናት ለአምሯዊ እና አካላዊ ጉዳቶች እየተጋለጡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.