Fana: At a Speed of Life!

ታዳጊ ልጆች የሳይበር ምህዳሩ ላይ ሊገጥማቸዉ የሚችሉ የጥቃት ተጋላጭነቶች

አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2014 (ኤፍ ቢሲ) ታዳጊ ልጆች በአሁኑ ጊዜ ከሳይበርና ከቴክኖሎጂ ነክ መገልገያዎች ጋር ከፍተኛ ግንኙነት እና መስተጋብር እንዳለቻው እርግጥ ነዉ ።

ታዲያ ይህ ቴክኖሎጂ ከሚሰጠዉ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ባሻገር በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲዉል ካልተደረገ በታዳጊ ልጆች ላይ በርካታ ጉዳቶችን ሊያስከትል ይችላል።

በመሆኑም ወላጆች እና አሳዳጊዎች ታዳጊ ልጆች ከቴክኖሎጂ ጋር ከሚፈጥሩት መስተጋብር ጋር ተያይዞ ሊደርሱባቸው የሚችሉ ጉዳቶችን በመገንዘብ ከፍተኛ ክትትል ሊያደርጉ ይገባል።

ታዳጊዎች በቀጥታ በበይነ-መረብ (ኦንላይን ) ቆይታቸው ሊያጋጥማቸው የሚችሉ ስጋቶች መካከል በበየነ መረብ የሚተላለፉ ተገቢ ያልሆኑ ይዘቶች ለምሳሌ የወሲባዊ ይዘት ያላቸው እርቃን ምስሎች እና ተንቀሳቃሽ ምስሎችን መመልከት፣ ዓመፅና የስቃይ ምስሎች እና ተንቀሳቃሽ ምስሎች፣ የወንጀል ቡድኖችን የሚደግፉ ይዘት ያላቸዉ መረጃዎች ፣ ህገወጥ ተግባር የሚያሳዩ ማስታወቂያዎች፣ ጽንፈኛ ድረገፆች፣ የሽብርተኛ ድርጅቶችን፣ ቦታዎችን ወዘተ መረጃዎች እና ፀያፍ ንግግሮችንና ጸያፍ ድርጊቶችን የሚጠቀሙ ይዘቶችን ከብዙ ጥቂቶቹ ናቸዉ ።

አንዳንድ የበይነ መረብ አዳኞች (predators) ወደ ቻት ሩም ወይም በማኅበራዊ የትስስር ገጾች ተጠቅመው ታዳጊ ህጻናትን ማግኘት ይችላሉ ፤ በእነሱ ዕድሜ ላይ የሚገኙ መስለው በመቅረብ ጓደኛ ይሆኗቸዋል ፤ አብዛኛውን ጊዜ ደግሞ እንደዚህ አይነት ሰዎች በአንድ ወቅት በአካል ለማግኘት ይሞክራሉ ብሎም በታዳጊዎች ላይ ተገቢ ያልሆነ ድርጊት ሊፈፅሙ ይችላሉ ።

ሌላኛዉ ደግሞ በማህበራዊ ሚዲያ የትስስር ገጾች አማካኝነት የሚደርስ የሳይበር ትንኮሳ ሲሆን፥ ህጻናት በማንነታቸዉ ምክንያት የሚደርስባቸው ዘለፋ እና ስድብ ነክ ትችት በስነ-ልቦናቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ከማድረስ አልፎ ራስን የመጥላት ብሎም ራስን የማጥፋት ስሜት ውስጥ ሊያስገባቸው ይችላል።

በተጨማሪም ብዙውን ጊዜ በበይነ መረብ ለሚሰነዘሩ ማጭበርበሪያዎች ዋነኛ ዒላማ የሚሆኑት አዋቂ ሰዎች እንደሆኑ ተደርገው ቢቆጠርም ታዳጊዎች ለዚህ አይነት ማጭበርበሪያዎች በጣም የተጋለጡ ናቸው።

ታዳጊዎችን በሚፈልጉት እና ሊያገኙት በሚፈልጉት ነገር ጋር በማያያዝ በሀሰት ሊጭበረበሩና ለከፋ ጉዳት ሊዳረጉ እንደሚችሉ የኢትዮጵያ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ባጋራው መረጃ አመላክቷል ።

በመሆኑም ወላጆች ታዳጊ ልጆቻቸው የበይነ መረብ ቀጥታ እንቅስቃሴ በሚያደርጉበት ወቅት ለሳይበር ትንኮሳ፣ መጭበርበር እና ግብረገብነት ለጎደላቸው ይዘቶች ተጋላጭ መሆናቸውን በመረዳት ለእነዚህ ጥቃቶች እንዳይጋለጡ ከፍተኛ የሆነ የቤተሰብ ክትትል ያስፈልጋቸዋል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.