Fana: At a Speed of Life!

አፍሪካ በፀጥታው ም/ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል-አፍሪካ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች

አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የተለያዩ አፍሪካ አገራት የዓለም አቀፍ ግንኙነትና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ገለጹ።
 
ለ35ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ አዲስ አበባ የተገኙ ታዳሚዎች እንደገለጹት፥አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል።
 
የደቡብ አፍሪካ ዓለም ዓቀፍ ግንኙነትና ትብብር ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶር፥ አፍሪካ እንደ አንድ ትልቅ አህጉር በጸጥታው ምክር ቤት መቀመጫ እንዲኖራት ያስፈልጋል ብለዋል።
 
በምክር ቤቱ ለውጥ ማምጣት ወሳኝና አስፈላጊ መሆኑን የደቡብ አፍሪካ ፅኑ እምነት መሆኑንም ገልጸዋል።
 
አፍሪካ ቋሚ መቀመጫ የሚያስፈልጋት ምክር ቤቱ ትልቅ የመወሰን አቅም ያለው ዓለም ዓቀፍ ተቋም ስለሆነ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
 
የናሚቢያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ዓለም አቀፍ ግንኙነትና ትብብር ሚኒስትር ኔቱምቦ ናንዲ ዳትዋ በበኩላቸው፥ አፍሪካ በተመድ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ሊኖራት ይገባል ብለዋል።
 
አፍሪካ ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራትና እንዲሁም በተለዋጭ አባልነት በመቀያየር አፍሪካን ይወክሉ ከነበሩት ሁለት አገራት ወደ አምስት ከፍ እንዲሉ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።
 
አፍሪካ ይህንን የፍትህ ጥያቄ ይዛ ቋሚ መቀመጫ ካላቸው አገራት ጋር የሚኖራት ንግግር ይቀጥላል ብለዋል።
 
የኡጋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሄኔሪ ኦሪየም፥ ተመድ ለአፍሪካ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ያለው ሁለት መቀመጫና ሁለት ደግሞ ተዘዋዋሪ መቀመጫ ሊሰጥ ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
 
አፍሪካ በአሁኑ ወቅት በተመድ ውስጥ ያለውን ኢፍትሃዊነት የመታገል መብት አላት ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፥ በአፍሪካ ሰላምና ደህንነት እንዲረጋገጥና የእርስ በርስ የንግድ ልውውጥ እንዲጠናከር አፍሪካዊያን ሊተባበሩ ይገባል ብለዋል።
 
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.