Fana: At a Speed of Life!

የሱዳን የፖለቲካ ኃይሎች ኢጋድ እንዲያደራድራቸው ፍላጎት አሳይተዋል

አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሱዳን የፖለቲካ ኃይሎች የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት /ኢጋድ/ እንዲያደራድራቸው ፍላጎት ማሳየታቸውን የተቋሙ ዋና ጸኃፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ገለጹ።

ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ እየተካሄደ ባለው 35ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን ኢጋድ የሱዳንን የፖለቲካ ቀውስ ለመፍታት እያደረገ ያለውን ጥረት አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ÷ ኢጋድ የሱዳን የፖለቲካ ቀውስን እልባት ለመስጠት የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ መቆየቱን ጠቁመው፤ በቅርቡም በኡጋንዳ ካምፓላ ከፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሜሲቬኒ ጋር ምክክር መደረጉን ተናግረዋል።

ውይይቱን ተከትሎም ኢጋድ ወደ ሱዳን ካርቱም በማምራት ከተለያዩ የሱዳን የፖለቲካ ኃይሎችና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ምክክር በማድረግ በኢጋድ ላይ ያላቸውን የመተማመን መንፈስ ለማወቅ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ጠቁመዋል።

በዚህም ሁሉም የሱዳን የፖለቲካ ኃይሎች ኢጋድ እንዲያደራድራቸው ፍላጎት እንዳላቸው ማረጋገጥ ተችሏል ነው ያሉት ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ።

ከዚህ ቀደም የተደረጉ ውይይቶች ጉዳዩን በሚመለከት ያለውን እውነት የማወቅ ተልዕኮ እንደነበራቸውም ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

አባል አገራት መሪዎች ጋር እውነትን የማወቅ ተልዕኮ ይዘው የተደረጉ ውይይቶችን በሚመለከት የተጠናከረውን ሪፖርት ላይ ውይይት መደረጉንም ገልጸዋል፡፡

በዚህም መሪዎቹ በኬንያ ናይሮቢ ተገናኝተው ለመወያየትና የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት ሥምምነት ላይ መድረሳቸውን አስረድተዋል።

የሱዳን የወቅቱ የኢጋድ ሊቀ መንበር መሆኗን አስታውሰው፤ በገጠማት የፖለቲካ ችግር ምክንያት የሊቀ-መንበርነት ሚናዋን ለሌላ የኢጋድ አባል አገር ማዘዋወር የሚያስችሉ ውሳኔዎች ሊኖሩ እንደሚችሉም ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.