Fana: At a Speed of Life!

የህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቆ የተሳተፉ መሪዎች በሰላም ወደ ሃገራቸው ተመልሰዋል – የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) 35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቆ በጉባኤው የተሳተፉ መሪዎችም በሰላም ወደ ሃገራቸው መመለሳቸውን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለፀ።

በጉዳዩ ላይ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ያወጣው መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፦

35ተኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቆ በጉባኤው የተሳተፉ መሪዎችም በሰላም ወደ ሃገራቸው ተመልሰዋል።

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድ አዳራሽ ተሰብስበው ስለ አፍሪካ የመከሩት የአፍሪካ ሃገራት መሪዎች፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና አምባሳደሮች ህብረቱ ዘንድሮ ካስቀመጠው መሪ አጀንዳ አንጻር የተቃኙ ውሳኔዎችንም አሳልፈዋል።

በተለይም አፍሪካ በአለም አቀፍ መድረኮች ተገቢውን ቦታ እንድታገኝ ለማድረግ ሁሉም ሃገራት በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባቸው መግባባት ላይ ተደርሷል ።

ከጉባኤው ጎን ለጎን በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ እና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በኩል ከተለያዩ ሃገራት መሪዎች ጋር የተካሄዱት የሁለትዮሽ ምክክሮች ኢትዮጵያ ከየሃገራቱ ጋር ያላትን ግንኙነት በልዩ ልዩ መስኮች ለማሳደግ የሚያስችሉ ናቸው።

ሃገራችን ኢትዮጵያ 35ተኛውን የአፍሪካ ህብረት ጉባኤን በተሳካና በደመቀ ሁኔታ አዘጋጅታ እንግዶቿን በሰላም ወደ ሃገራቸው ሸኝታለች።

አሁንም ከፍተኛ የጤና ስጋት የሆነውን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል የገባችውንም ቃል አክብራ ጉባኤው ከመጀመሩ አስቀድሞ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ዘርፈ ብዙ የጥንቃቄ እርምጃዎችን ወስዳለች።

ይህ ጉባኤ በህብረቱ ዋና መቀመጫ በሆነችው በአዲስ አበባ እንዳይካሄድ የነበሩ ጫናዎችን ሁሉ በመቋቋም ከእስከዛሬው በተለየ ድምቀት ጉባኤውን ያለ ምንም እክል ማስተናገድ መቻሏ ለኢትዮጵያና ለመላው ኢትዮጵያውያን ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ድል ነው።

35ተኛው የአፍሪካ ሀብረት የመሪዎች ጉባኤ፤ የኢትዮጵያን በጎ የማይመኙ አካላት ሲሉት እንደነበረው ሳይሆን ሃገራችን በሰላማዊ መንገድ ፍዑም ኢትዮጵያዊነት በተሞላበት የእንግዳ አቀባበል ስርአት ማንኛውንም አህጉራዊና አለም አቀፍ ሁነት በተሳካ ሁኔታ ማስተናገድ እንደምትችልም ዳግም ያስመሰከረችበት ነው።

ለዚህ መሳካት አስተዋጽኦ ያደረጋችሁ የጸጥታ አካላት፣ መገናኛ ብዙሃን፣ አገልግሎት ሰጪዎች ባጠቃላይ እንግዶች ወደ ሁለተኛ ቤታቸው የመጡ ያህል እንዲሰማቸው ያደረጋችሁ ሁሉ በተለይም መላው የአዲስ አበባ ነዋሪ፤ በጉባኤው ምክንያት የተፈጠሩ የመንገድ መጨናነቅና አንዳንድ ክለከላዎች ሳያማርሯችሁ በታላቅ ኢትዮጵያዊ ጨዋነት፣ በትዕግስትና በሞቀ የእንግዳ አቀባበል ስሜት ከጉባኤው መጀመሪያ እስከ መጨረሻ ላበረከታችሁት አስተዋጽኦ መንግስት ላቅ ያለ ምስጋናውን ያቀርባል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.