Fana: At a Speed of Life!

ሚኒስቴሩ የመልሶ ማቋቋሚያ እቅድ በማውጣት የወደሙ የባህልና ስፖርት ተቋማትን ወደ ስራ ለማስገባት በትኩረት መስራት አለበት- ቋሚ ኮሚቴው

አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የመልሶ ማቋቋሚያ እቅድ በማውጣት በአማራና አፋር ክልሎች የወደሙ የባህልና ስፖርት ተቋማትን ወደ ስራ ለማስገባት በትኩረት መስራት እንዳለበት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ፡፡
 
በምክር ቤቱ የጤና፤ ማህበራዊ ልማት ፤ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴርን የ2014 በጀት ዓመት የ6 ወር እቅድ አፈጻፀምን ገምግሟል፡፡
 
በዚህም ቋሚ ኮሚቴው በአማራ እና በአፋር ክልሎች የወደሙ ባህላዊ እሴቶች፣ ታሪካዊ የቱሪስት መዳረሻዎች ፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የወጣቶች ስብዕና መገንቢያ ማእከላት ሌሎች ተቋማትን መልሶ ለመገንባት በትኩረት እንዲሰራ መመሪያ ሰጥቷል፡፡
 
የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር ቤተልሄም ላቀው÷ ሚኒስቴሩ እስካሁን ባለው ሂደት የመልሶ መቋቋሚያ እቅድ አዘጋጅቶ ለቋሚ ኮሚቴው አለማቅረቡን ተናግረዋል፡፡
 
ሚኒስቴሩ ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች ላይ በሚገባው ልክ የመስክ ምልከታ አለማድረጉን ያነሱት ዶ/ር ቤተልሄም÷እቅዱን በ15 ቀናት ውስጥ በማዘጋጀት ለቋሚ ኮሚቴው እንዲያቀርብም አስገንዘበዋል፡፡
በተጨማሪም ኀብረተሰቡ ከእደ-ጥበብ ዘርፍ ተጠቃሚ እንዲሆን እስከታችኛው መዋቅር ያሉ የሚኒስቴሩ አደረጃጀቶች ተገቢውን ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
 
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጄላ መርዳሳ÷ በጦርነቱ ሳቢያ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለማቋቋም ከፍተኛ ወጪ እንደሚጠይቅ ጠቅሰው÷ሚኒስቴሩ በቋሚ ኮሚቴው የተነሱ ሃሳቦችን እንደግብዓት በመውሰድ በቀጣይ ለማረም እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡
 
ሚኒስቴሩ በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል አዲስ ተቋማዊ አደረጃጀት እየሰራ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡
 
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
 
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.